ETHIOREVIEW

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሃርጌሳ ገቡ – ሶማሌ በረራ አስተጓጎለች

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሀርጌሳ ገቡ፤ የባህር በር ስምምነቱና ርክክቡ ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከተለያዩ ወገኖች መረጃ እየወጣ ሲሆን የሞቃዲሾ ባለስልጥናት ቻርተርድ የሆነው አውሮፕላን እንዲመለስ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ያለው ነገር የለም። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አንድ አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ እንዲመለስ ማደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካተተ ልዑክ ሃርጌሳ መድረሱን ከሶማሊ ላንድ የወጡ የቪዲዮ መረጃዎች አሳይተዋል። አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ሀርጌሳ ኢጋል አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም ማረፉን አየር ማረፊያው አመልክቷል።

በሃርጌሳ ከተማ በኢትዮጵያ ልዩ የኮማንዶ ሃይሎች የታጀቡ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተከታታይ በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ ሲያመሩ የሚያሳየው ቪዲዮ ባለስልጣናቱ ሃርጌሳ መገባታቸውን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ከዛው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

አቀባበሉና የጎዳና ላይ አጀቦች እንደሚያሳዩት ከሆነ በከተማዋ የተዘጋ ጎዳና አልታየም። በጎዳናዎቹ ላይ የተለመደው መደበኛ የተሽከርካሪዎች እንቃቃሴም ይታይ ነበር።

ከሳምንት በፊት የሁለቱ አገራት የመከላከያ ኤታማዦር ሹሞች በአዲስ አበባ ተገናኝተው መምከራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ኤርትራ በይፋ ኢትዮጵያን መቃወሟባ ከሞቃዲሾው መንግስት ጋር እንደምትቆም ማስታወቋ አይዘነጋም። በኢትዮጵያና በሰላም አስከባሪዎች ሃይል የሚንቀሳቀሰው የሞቃዲሾው መንግስትም ዛቻ ሲያሰና ነበር።

በመንግስት ደረጃ መግለጫ ያልሰጠችው አሜሪካ በጋዜጠኞች መድረክ ላይ ስጋት እንዳላት ገልጻለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ ለቀጣናው ሰላም መከበር ከቀድሞ በበለጠ አበክራ እንደምትሰራ፣ የባህር በር ባለቤ መሆኗ ደግሞ ለቀጣናው ሰላምና ተያይዞ የማደግ እድል መልካም አጋጥሚ እነደሚሆን ደጋግማ እያስራወቀች ነው። የኤርትራን ተቃውሞ አስምልክቶ ህዝብ ጉምጉምታ እያሰማ ነው።

ይህ በንዲህ እንዳለ ነው የባለስልጣናቱ ጉዞ ከወር በሁዋላ ተግባራዊነቱ ይፋ እንደሚሆን የተነገረለትን የኢትዮጵያን ባህር በር ባለቤት የሚያደርገው ስምምነትና የሶማሊላንድን ጥቅም ላይ ይፋዊ ስምምነት ለማድረግ እስፍራው ዘንድ ያቀናው። ስምምነቱም ይፋ እንዲሆን የሚስችሉ የመጨረሻ ውል እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል።፣ ሁሉንም ጉዳይ ወደ ተግባር የሚቀይረው ሰነድ መቋጫ እንደሚበጅለት ለመረጃው ቅርብ የሆኑ አስታውቀዋል።

በዕለቱ የተለያዩ በረራዎች እንደነበሩ አስታውሶ ቢቢሲ የዘገበው ከታች ተመልክቷል።

በዛሬው እለት ቀኑን ሙሉ ሞቃዲሾን ቢዚ ያደረገ የበረራ ድራማዎች የነበሩ ሲሆን በመጨረሻም ጉዳዩ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

ወደ ሶማሊላንድ መዲና ሃርጌሳ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የሶማሊያ አየር ክልል ውስጥ ከመግባቱ በፊት እንዲመለስ መደረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሃርጌሳ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን ከሶማሊያ በኩል ፍቃድ የለውም በመባሉ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ለማረፍ ተገዷል።

“ወደ ሃርጌሳ እየሄደ የነበረው አውሮፕላን ተመልሷል። ምክንያቱም በረራውን ከጀመረ በኋላ ከሶማሊያ በኩል ፍቃድ አልሰጠንም የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነው” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

የበረራ መከታተየ በሆነው ፍላይትራዳር24 በተባለው ድረ ገጽ ላይ መመልከት እንደሚቻለው ዛሬ ጥር 8/2016 ዓ.ም. ሁለት በረራዎች ወደ ሶማሊያ ተደርገዋል።

መደበኛው የበረራ ቁጥር ኢቲ372 ረፋድ 5 ሰዓት ላይ ሃርጌሳ ማረፉን ፍላይትራዳር ያሳያል።

ይሁን እንጂ የበረራ ቁጥር ኢቲ8372 የሆነው ዲ ሃቪላንድ-400 አውሮፕላን ጠዋት 2፡30 ከአዲስ አበባ ተስቶ ወደ ሃርጌሳ አቅጣጫ እየበረረ ሳለ የጂግጂጋ ሰማይ ላይ በመዞር ረፋድ 4፡30 አካባቢ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተመልሶ አርፏል።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ዘግይቶ በወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ8372 ፍቃድ ስላልነበረው ሃርጌሳ ላይ እንዳያርፍ መከልከሉን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ እንዳለው የኢቲ 8273 በረራ ከሶማሊያ ማግኘት የነበረበትን ፈቃድ ስላልነበረው የዓለም አቀፍ የበረራ ሕግን በመተላለፉ ወደ አገሪቱ የአየር ክልል እንዳይገባ መደረጉን ገልጿል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው የትኛው የአየር መንገዱ አውሮፕላን እንዲመለስ እንደተደረገ እና እንዲመለስ በተደረገው አውሮፕላን ተሳፍረው ስለነበሩት መንገደኞች ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይሁን እንጂ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይሳ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የያዘ አውሮፕላን ፍቃድ ስላልነበረው ወደ ሃርጌሳ እንዳይገባ ተከልክሏል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው እንዲመለስ የተደረገው ልዩ [ቻርተርድ] በረራ ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገረ ሲሆን የአየር መንገዱ መደበኛ በረራዎች ግን መቀጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ከተደረገው አውሮፕላን ውጪ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረጉት መደበኛ በረራዎች መቀጠላቸውን አረጋግጧል።

ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ውጥረት ሰፍኗል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሠነድ ተፈጻሚ ሲሆን በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የባሕር ጠረፍ የሚያስገኝላት ሲሆን፣ በምላሹም ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ይህን ስምምነት መፈራረማቸውን ሶማሊያን በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን፣ በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ አጥብቃ ተቃውማዋለች።

ይህ ክስተቱም ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ፖለቲካዊ ውጥረትን ፈጥሯል።

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቀደም ብሎ ደግሞ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያን የሶማሊያ “ጠላት” ሲሉ ገልጸዋት ነበር።

Exit mobile version