Site icon ETHIOREVIEW

የትራምፕ ዋንኛ ተቀናቃኝ ‘በቃኝ!’ አሉ

የሪፐብሊካን እጩ ሆኖ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ከፍተኛ ፉክክር ላይ የነበሩት የፍሎሪዳ ገዥ ሮን ዲሳንተስ ከውድድር ወጥቻለሁ አሉ።

ዲሳንተስ የትራምፕ ከፍተኛ ተቀናቃኝ የነበሩ ናቸው። ሮን ዲሳንተስ ከውድድር በበቃኝ መውጣት ብቻም ሳይሆን ለወራት ሲያንጓጥጧቸው የነበሩትን ትራምፕን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። የዲሳንተስ ለትራምፕ ድጋፍ መስጠት በውድድሩ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል። ዲሳንተስ በቃኝ ያሉት ዛሬ ማክሰኞ በኒው ሐምፕሻየር ግዛት ድምጽ ሊሰጥ በሚጠበቅበት ዋዜማ ነው።

ሮን ዲሳንተስ ከሳምንት በፊት በአዮዋ ግዛት በተሰጠ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ድምጽ አሰጣጥ 2ኛውን ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸው አስፈንድቋቸው ነበር። ደጋፊዎቻቸውም ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር። ይህ የሆነው ከትራምፕ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኛሉ ተብለው የተጠበቁት አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ስለነበሩ ነው። ኒኪ በትራምፕ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር እንደነበሩ ይታወሳል። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የሳውዝ ካሮላይና ግዛት ገዢ ነበሩ።

ከ10 ወራት በኋላ በኅዳር፣ 2017 ዓ.ም በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ዶናልድ ትራምፕ በተለይ በሪፐብሊካኖች ዘንድ አሁን አሁን ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ ነው። ለዚህም ማሳያ ባለፈው ሳምንት በአዮዋ ግዛት በተደረገ ምርጫ ያገኙት ድምጽ አንድ ምልክት ነው። ሁሉም ተቀናቃኝ እጩዎች ያገኙት ድምጽ ተደምሮ ትራምፕ ካገኙት ድምጽ ያነሰ ነበር።

የፍሎሪዳው ገዢ ሮን ዲሳንተስ ከዓመት በፊት ቀጣይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሰው ነበሩ። ለውድድሩ የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻሉትም ቀደም ብለው ነበር። በዚህ ፍጥነት ከውድድሩ ይወጣሉ ተብሎ ያልተጠበቀውም ለዚሁ ነው።

ያለፈው እሑድ እለት ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በበቃኝ መውጣታቸውን የሰሙት ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ አመስግነዋቸዋል። አምስት ደቂቃ በወሰደውና በትዊተር (ኤክስ) ማሀበራዊ ድረ-ገጽ በተላለፈው የዲሳንተስ የበቃኝ ንግግር ብዙ ሪፐብሊካኖች ከኔ ይልቅ ትራምፕ ሁለተኛ ዕድል እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ተረድቻለሁ፤ ስለዚህ ራሴን ከውድድር አግልያለሁ ብለዋል።

በዲሞክራቲክ ፓርቲ በኩል አሁን ለፕሬዚዳንትነት አዲስ እጩ ሊታይ የሚችልበት ዕድል እየተመናመነ ይመስላል። ብቸኛው ተወዳዳሪም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይሆናሉ። ጆ ባይደን በተለይ ከእድሜያቸው መግፋት የተነሳ በገዛ ፓርቲ ሰዎቻቸው ሳይቀር በዚህ ውድድር እንዳይሳተፉ ግፊት ሲደረግባቸው ነበር።

ጆ ባይደን ግን ዐይኔ እያየ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ አይመለስም፤ ዲሞክራሲያችንን መጠበቅ አለብን በሚል በአቋማቸው ጸንተዋል። ያለፈው እሑድ ከሰዓት የምረጡኝ ቅስቀሳ በኒው ሐምፕሻየር ግዛት ሲያደርጉ የነበሩት ትራምፕ የተቀናቃኛቸውን የዲሳንተስን ከውድድር መውጣት ይፋ ሲያደርጉ ደጋፊዎቻቸው በሆታ ደስታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ትራምፕ ከአፍታ በኋላ ዲሳንተስ ብርቱ ሰው ነበር፤ ብዙ ርቀት ሄዷል፤ ሊደነቅ ይገባል በማለት አዎንታዊ አስተያየት ሰጥተዋል። ትራምፕ ለወራት ተፎካካሪያቸው ዲሳንቲስን “ቀሽም፣ አስቀያሚ፣ ከንቱ፣ እኔ ከትቢያ አንስቼ ሰው ያደረኩት፣ የእናት ጡት ነካሽ “ እያሉ ሲያብጠለጥሏቸው እንደነበር ይታወሳል።

በርካታ የሪፐብሊካን ደጋፊዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዲሳንተስ ጥሩ እጩ ቢሆንም አሁን የሱ ጊዜ አይደለም ብለዋል። የትራምፕ የዋይት ሐውስ ጉዞ ምናልባት እየቀረቡባቸው ባሉ በአራት መዝገብ በተዋቀሩ 91 ተደራራቢ ክሶች የማይጨናገፍ ከሆነ ሊሰምር የተቃረበ ይመስላል።

በተለያዩ ድርጅቶች የተሠሩ የሕዝብ ትርታን የሚፈትሹ የዳሰሳ ጥናቶች እንዳሳዩት ጆ ባይደን ድጋፋቸው እየተሸረሸረ ነው። ይህም በዋናነት በአሜሪካ በተከሰተ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የዩክሬንና የጋዛን ጦርነት ማስቆም ባለመቻላቸው፣ እንዲሁም በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሜክሲኮ ድንበር በየቀኑ እየገቡ መሆኑና ይህን ማስቆም ባለመቻላቸው ነው።

ትራምፕ በበኩላቸው እኔን ከመረጣችሁኝ የነዳጅ ዋጋን አረጋጋለሁ፤ በተመረጥኩ በማግስቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የማባረር ሥራ እጀምራለሁ፤ የዩክሬንን ጦርነት በፍጥነት አስቆማለሁ በሚል ከወዲሁ ቃል እየገቡ ነው። ትራምፕ አራት ጊዜ በወንጀል ተከሰዋል። እጅግ በርካታ የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች ይጠብቃቸዋል። ይሁንና የክስ ሂደቶቹ ትራምፕን ከምርጫ እንደማያግዳቸው በተደጋጋሚ አሳውቀዋል።

በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ ሀገራት ምርጫ ይደረጋል። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ብዛት ያላቸው ድምጽ ሰጪዎች፣ በመላው ዓለም ወደ ተዘጋጁ የምርጫ ጣቢያዎች ይጎርፋሉ ተብሏል። አራት ቢሊዮን የሚሆነው ወይም ከዓለም ሕዝብ ግማሹ፣ ወደ ምርጫ ጣቢያ በማቅናት ድምጽ እንደሚሰጥ ይገመታል።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥር  14/2016

Exit mobile version