ETHIOREVIEW

በግብጽ ምሪት “ጦርነቱ የማይቀር ነው” ያለችው ሶማሊያ አቅሟ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር

ሶማሊያ በአልሸባብ የሽብር ጥቃት ስትወላልቅና፣ ዜጎቿ ሲጨፈጨፉ፣ ያልሞቱትም የቁም ስቃይ እያዩ ሳለ አንድም ቃል ተንፍሳ የማታውቀው ግብጽ “ዘራፍ” እያለች ነው። የሶማሊያን መሪ ከፊት አድርጋ የጦርነት እስክስታ እየወረደች ያለችው ግብጽ ” አለሁበት” ስትል በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ በስማሊላንድ የጦር ሰፈር እንዳታቋቁም ድጋፍ እንደምትሰጥ ማስታወቋ ይታወሳል።

ለዚህ ይመስላል አቶ ሬድዋን ሁሴን ” … ለሶማሊያ በችግሯጊዜ ብዙ ድጋፍ ያላደረጉ አንዳንድ ተዋናዮች ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ወዳጆቿ ለማሳየት እየሞከሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ያነሳሳቸው ለሶማሊያ ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ መሆኑ ግልጽ ነው። ” ሲሉ በግል የመረጃ ሳጥናቸው በኤክስ በኩል የገለጹት።

በእጅ ጣት የቆጠራ ምርጫ የተመረጡት የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከግብፅ መንግሥት በቀረበላቸው ግብዣ ወደ ካይሮ ካመሩ በሁዋላ በዝግ መክረው ሲጨርሱ ” እስካሁን ድንበራችንን አልወረረችም፤ ከወረረች ግን ይለይልናል” ሲሉ ለግብጽ ሚዲያ በይፋ ውጊያ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ ዛቻቸውን የሰሙ ” ሰውየው ጤነኛ አይደሉም እንዴ” ሲሉ እየተዛበቱባቸው ነው። በኢትዮጵያ ወታደሮችና ድጋፍ ተኝተው እንደሚያድሩ የሚጠቅሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ “ለመሆኑ ጦርነት ቢነሳ ሶማሊያ እንዴት ኢትዮጵያን ትቋቋማለች?” ሲሉ የተለያዩ መረጃዎችን ጠቅሰው መሬት ላይ ባለ እውነት ሚዛንኑን ያሳያሉ። ለአብነት ቢቢሲ ከተለያዩ መረጃዎች ሰብስቦ ያቀረበውን ያጣቅሳሉ። ከስር ያንብቡ

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ወታደራዊ ደረጃ

በተለያዩ ጦርነቶች ውስጥ የቆዩት ሁለቱ አገራት ተመጣጣኝ ያለሆነ የሠራዊት እና የትጥቅ አቅም እንዳላቸው የአገራትን አቋም ይፋ የሚያደርገው የዓለም አቀፉ ተቋም መረጃ ያመለክታል።

የአገራትን አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም በመመዘን ደረጃን የሚሰጠው ግሎባል ፋየር ፓዎር፤ በ2024 ዕትሙ የ145 አገራትን ከሠራዊት ብዛት እስከ ትጥቃቸው ድረስ ወታደራዊ አቅምን ፈትሿል።

በዚህ መሠረት ግሎባል ፋየር ፓወር ኢትዮጵያ ከ145 አገራት 49ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ሶማሊያን 142ኛ ደረጃን ሰጥቷል።

በዚህ ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከአፍሪካ አገራት አንጻር ሲታዩ እጅግ በተራራቀ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅም በአህጉሪቱ ካሉ 54 አገራት መካከል የአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ከፊቷ የሚገኙት ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ናቸው።

በግሎባል ፋየር ፓወር ደረጃ መሠረት ከሶማሊያ ኋላ የሚከተሉት ሱሪናም፣ ሞልዶቫ እና ቡታን በመሆናቸው በአፍሪካ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ትቀመጣላች።

የ145 አገራትን ወታደራዊ አቋም በመመዘን በየዓመቱ ደረጃ የሚያወጣው ግሎባል ፋየር ፓወር፣ ለምዘናው 60 ያህል የመገምገሚያ ነጥቦችን ይጠቀማል።

እነዚህ መመዘኛዎችም አገራት ያሏቸው ወታደራዊ ክፍሎች ብዛት፣ ለሠራዊታቸው የሚመድቡት ዓመታዊ በጀት፣ ለሠራዊታቸው የሚያስፈልጉትን አቅርቦቶች በተገቢው እና በአስፈላጊው ጊዜ በማቅረብ እንዲሁም አገራቱ ካላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር በዝርዝር ተገምግመዋል።

እስኪ የኢትዮጵያን እና የሶማሊያን ሠራዊት የወታደር፣ የመሳሪያ፣ የአቅርቦት እና የበጀት አጠቃላይ መጠንን ለንጽጽር እንመልከት።

የሰው ኃይል

ኢትዮጵያ 116 ሚሊዮን አጠቃላይ ሕዝብ ያላት ሲሆን፣ ከዚህ መካከል ለወታደራዊ ዘመቻ ብቁ የሆነ 34.7 ሚሊዮን ሕዝብ አላት።

በአንጻሩ ሶማሊያ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 12.6 ሚሊዮን ሲሆን፣ ለወታደራዊ ዘመቻ ብቁ የሆነው የሕዝብ ቁጥሯ 1.7 ሚሊዮን ነው።

እንደ ግሎባል ፋየር ፓወር አሃዝ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል 162 ሺህ የሚሆን አጠቃላይ የሠራዊት ብዛት ያለው ሲሆን፣ በአንጻሩ ሶማሊያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሏን ጨምሮ የሠራዊቷ ቁጥር ከ17 ሺህ የሚሻገር አይደለም።

የሠራተኛ ኃይል፣ ፋይንስ እና ሎጂስቲክ

ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ በሚካሄድ ጦርነት ውጤት ላይ የአንድ አገር ንቁ ተሳታፊ የሆነ ሠራተኛ ብዛት ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ግሎባል ፋየር ፓወር በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ እና በጦር ሜዳ ውሎ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ተተኳሽ፣ የደንብ ልብስ፣ መለዋወጫዎች፣ መድኃኒት፣ ምግብ. . . እና የመሳሰሉትን የሚያመርተው ሠራተኛ ኃይል ወሳኝ ነው ይላል።

ኢትዮጵያን ይህን የመከወን አቅም ያለው 56 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የገለጸ ሲሆን፣ በአንጻሩ ሶማሊያ ያላት የሠራተኛ ኃይል ቁጥር 3 ሚሊዮን ገደማ ነው።

በአንድ ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ የፋይናንስ አቅም እና እንደ ነዳጅ ያሉ የሎጂስቲክ አቅርቦቶች ለሠራዊቱ እንቅስቃሴ እና ውጤታማነት መሠረታዊ ናቸው።

ግሎባል ፋየር ፓወር እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ለጦር ሠራዊቷ ከ888 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ በጀት የምትመድብ ሲሆን፣ ሶማሊያ በአንጻሩ ዓመታዊ በጀቷ 458 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች፣ ጦር አውሮፕላኖች . . . አጠቃላይ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች 110 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ የሶማሊያ ጦር ግን የሚፈልገው ዓመታዊ የነዳጅ መጠን ግን 6 ሺህ በርሜል ነው።

የአየር እና ባሕር ኃይል

ግሎባል ፋየር ፓወር እንደሚለው ከሆነ ኢትዮጵያ 91 ወታደራዊ አውሮፕላኖች አሏት። ከእነዚህ መካከል 23 ተዋጊ ጄቶች ናቸው።

በተጨማሪም የጠላትን ዒላማ የሚመቱ እንዲሁም በጦር ሜዳዎች የቅኝት ሥራ የሚያከናውኑ፣ የተጎዱ የሚያነሱ፣ ልዩ ወታደራዊ ግዳጆችን የሚደግፉ እና የመሳሰሉትን የሚሰሩ 37 ሄሊኮፕተሮች አሏት።

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ለሥልጠና የሚውሉ 37 የተለያዩ መጠን ያላቸው አውሮፕላኖችም አሏት።

በዚህ እአአ 2024 በተሻሻለው የግሎባል ፋየር ፓወር ሪፖርት ላይ ባይጠቀስም ኢትዮጵያ ትንሽ የማይባል ቱርክ፣ ቻይና እና ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እንዳላት ይታመናል።

በአንጻሩ ሶማሊያ ተዋጊም ሆነ የትራንስፖርት እንዲሁም ለሥልጠና አገልግሎት የሚውሉ ምንም አይነት የጦር አውሮፕላኖች እንደሌላት የግሎባል ፋየር ፓወር ሪፖርት ያሳያል።

በዚህ ሪፖርት ላይ በወታደራዊ አቅም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ተሽላ የተገኘችው በባሕር ኃይል አቅም ነው። ሶማሊያ እንደ አውሮፕላን ተሸካሚ የመሳሰሉ ገዙፍ መርከቦች ባይኖሯትም፣ በዚህ ሪፖርት ላይ አቅማቸው በግልጽ ያልተጠቀሰ 11 የባሕር ላይ ቅኝት የሚያደርጉ መርከቦች አሏት።

የባሕር በር አልባዋ ነገር ግን ባሕር ኃይሏን መልሳ እየገነባች የምትገኘው ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ዘመቻን የሚወጡ ምንም አይነት የባሕር ኃይል መርከቦች የሏትም።

ሲያድ ባሬ የገነቡት የሶማሊያ ጦር ከኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በኋላ እንዲሁም የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሠራዊት ፈርሶ መቆየቱ ይታወቃል።

ከለውጡ በሁዋላ ኢትዮጵያ የገነባችው የባህር ሃይል ትጥቅና አቅም በሪፖርቱ አልተካተተም። ባህር ሃይል ልክ እንደ አየር ሃይል አመዱን አራግፎ ዳግም ሲመሰረት ኢትዮጵያ ከፈረሳይና ከሩስያ ግዙፍ የጦር መርከቦችን መግዛቷ መገለጹ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ብቁ የባህር ሃይል እንዳላትና እነሱም ውጭ አገር ድረስ ሄደው ሰልጥነው የመጡ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይገለጻል።

Exit mobile version