Site icon ETHIOREVIEW

52 የመንገድ ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር ቆመዋል፤ የታገቱና የተገደሉ ባለሙያዎች አሉ

ባለሙያዎችን መግደል፣ ማገት፣ ፕሮጀክት ማስተጓጎል የዘመኑ የኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ውጤት ሆኗል። ከዚህ ዓይነቱ የትግል ስልት የሚጎዱው ህዝብና አገር መሆኑ ግልጽ ነው። ቸግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ በርካቶች ሁሉንም ወገን የሚወተውቱት ለዚህ ነው። ከመንገድ ጋር በተያያዘ የቀረበው ሪፖርት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። ሪፖርተር ያልተሳካውን ነቅሶ የዘገበውን ያንብቡ

በፀጥታ ችግር 52 የመንገድ ፕሮጀክቶች መቆማቸው ተጠቆመ።  ከፕሮጀክት አስተዳደር ኃላፊዎች መካከል ታግተው መለቀቃቸውን፣ መንገድ ላይ በሽፍታ መዘረፋቸውን፣ በጉባ ድልድይ አራት መሐንዲስና ዘጠኝ ባለሙያዎች መገደላቸው፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለ2016 በጀት ዓመት ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከጠየቀው ሲሚንቶ ማግኘት የቻለው 14 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ከተጠየቀው 682,085 ቶን ሲሚንቶ ማግኘት የተቻለው 95,610 ቶን ወይም 14 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሪፖርት ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ አስተዳደሩ ለግንባታ ግብዓትነት ከጠየቀው 202,315,139 ሊትር ነዳጅ ውስጥ ማግኘት የቻለው 79,446,433 ሊትር ወይም 39 በመቶ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ችግሩ ስራውን እንዳወከው ገለጸው ፣መንግሥት ለህዳሴው ግድብ በሚያቀርበው ሁኔታ እንዲያቀርብልን ጠየቀው እንዳልተሳካ አመልክተዋል። በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያስፈልገንን ምርት ለማግኝት የሚያስችል ተስፋ መኖሩንም አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የአስፋልት (ሬንጅ) እጥረት ማጋጠሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ የነበረው አስተዳደሩ፣ ባለፉት ስድስት ወራት 22,000 በርሜል አስፋልት በአገር ውስጥ ግዥ፣ እንዲሁም 70,000 በርሜል ከውጭ አገር ግዥ ለማከናወን በሒደት ላይ መሆኑን የጠቀሱት መሐመድ (ኢንጂነር) አምልክተዋል። 10,000 በርሜል አስፋልት አገር ውስጥ ገብቶ ለዲስትሪክቶች መሠራጨቱን ተናግረዋል፡፡

ከ238 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶችእንዳሉት የገለጸው አስተዳደሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች የግብዓት እጥረትን በሚመለከት ከሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር፣ ከማዕድን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁን እንዳልተቀረፈ በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

አስተዳደሩ ከግብዓት እጥረት በተጨማሪ በመላ አገሪቱ ካሉት 25 የፕሮጀክት ቢሮዎች 48 በመቶ በፀጥታ ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውን፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጂነር ደጀኔ ፈቃደ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት ከፕሮጀክት አስተዳደር ኃላፊዎች መካከል ታግተው መለቀቃቸውን፣ መንገድ ላይ በሽፍታ መዘረፋቸውን፣ በጉባ ድልድይ አራት መሐንዲስና ዘጠኝ ባለሙያዎች መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡

በየጊዜው የሕይወት መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው ያሉት ደጀኔ (ኢንጂነር) በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ሠራተኞች በፕሮጀክት ተሽከርካሪ ብቻቸውን መሄድ ባለመቻላቸው፣ ከሕዝብ ጋር በቅጥቅጥ አውቶቡስ ወይም በሚኒባስ በመሄድ ፕሮጀክቶችን እየተከታተሉ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እያስተዳደርን ያለው ፕሮጀክት ሳይሆን ቀውስ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶች ብዛት 52 መሆናቸውንና ከእነዚህ መካከል በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ ቄለምና ሆሮ ጉዱሩ የወለጋ ዞኖች የሚገኙ ፕሮጀክቶች፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ ባቱ፣ አርሲ ነገሌ፣ ቢልባላ፣ ሰቆጣ፣ ክምር ድንጋይ፣ ጉና፣ እስቴ ስማዳ፣ ጊንጪ ሽኩቴ፣ ሻምቡ አጋምሳ፣ ሻምቡ አጋምሳ፣ ደብረ ማርቆስ ሞጣ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ከተቋረጡ 32 ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ  አዲአርቃይ ጠለምት፣ ጋሸና ቢልባላ፣ ጥቁር ውኃ ሐዋሳ፣ ውቅሮ አፅቢ ኩናባ፣ ኮረም ላሊበላ፣ ዓዲሸሁ ደላ ሳምረ፣ ማይጨው መኾኒ፣ ዓዲሸሁ ደላ ሳምረ፣ ማይጨው መኾኒ፣ ፍየልውኃ ተከዜና ሌሎችም እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

በዋነኛነት በፕሮጀክቶች አካባቢና በፕሮጀክቶች መዳረሻ (Logistic Corridor) የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች በፕሮጀክቶች ቀጥታ አፈጻጸም ላይ፣ እንዲሁም በግብዓት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ፎቶ – ሪፖርተር ጋዜጣ

Exit mobile version