ETHIOREVIEW

የምግብ ሉዓላዊንት – አብይ አህመድ በተመድ የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸለሙ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሽልማት የተሰጣቸው ዛሬ በጣልያን፤ ሮም ከተማ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO) ፤ ሮም ውስጥ ባሰናዳው ዝግጅት ዶ/ር ዐቢይ ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያደረጉ ላለው ጥረት የከበረውን አግሪኮላ ሜዳልያ እንዳበረከተላቸው ተነግሯል።

የፋኦ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኩ ዶግዩ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፋኦ ከፍተኛ ሽልማት ለሆነው አግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማት በመብቃታቸውን ” እንኳን ደስ አልዎት ! ” ብለዋቸዋል።

ይህ ሽልማት መሪዎች እና ሌሎችም የዓለማችን እውቅ ሰዎች የምግብ ዋስትናናን ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ድህነትን ለመቀነስ ለሚያደርጉት የተሳካ ጥረት የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም የአግሪኮላ ሜዳሊያ ለጠ/ ሚኒስትሩ እየተበረከተው ፦

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ራዕይ ኢትዮጵያን የብልፅግና ብቻ ሳይሆን የውበት ተምሳሌት እንደሚያደርጋት እርግጠኛ ነኝ፡- የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩን

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ራዕይ ኢትዮጵያን የብልፅግና ብቻ ሳይሆን የውበት ተምሳሌት እንደሚያደርጋት እርግጠኛ ነኝ ሲሉ የተመድ የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩን ተናገሩ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገጠር ልማትን መሰረት ያደረገ ታላቅ ራዕያቸውን በአድናቆት ተመልከተውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዓለማቸውን ተገባራዊ ለማድረግም በቁጠኝነት እና በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲሰሩ እንደነበር መገንዘባቸውንም የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ እያደረጉት ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ አስደሳች ውጤት እንዳስመዘገበች ገልጸዋል፡፡

ዶንግዩን አክለውም “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ራዕያቸውን ከግብ እንደሚደርሱም እርግጠኛ ነኝ፤ እሳቸው የጀመሩት ተግባር መጪውን የኢትዮጵያ ጊዜ የብልፅግና ብቻ ሳይሆን የውበት እና የአረንጓዴ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል” ብለዋል፡፡

ለዚህ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አርአያነት ያለው ተግባርም ታላቁን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማት ሲያበረክቱ ክብር እንደሚሰማቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

“ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን እና ለሌላው ዓለም አርአያ የሚሆን ነው” የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩን

********

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን እና ለሌላው ዓለም አርአያ የሚሆን

ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማት ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገሪቱ መሪ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ለግብርናው ምርታማነት ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነት እንዲያድግ ያደረጉት ጥረት እና ያስገኙት ውጤት፤ ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መኖሩን ጭምር ያረጋገጠ እንደነበር መስክረዋል፡፡

“ለአፍሪካውያን አሁን በእርግጠኝነት መናገር የምፈልገው ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መኖሩን ጭምር ነው፤ ይህንን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስንዴን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ጭምር በተግባር አሳይተውናል፡፡” ብለዋል የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩን።

ባለፉት 5 ዓመታት ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸው የገለጹት ዋና ዳይሬከተሩ በተለይም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርታማነት ያስመዘገበችው ውጤት እኔ እማኝ መሆን እችላለው በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡

አብይ ምን አሉ?

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ታደርጋለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ረሀብን ዜሮ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።

የዕውቅና ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተላቸው በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆኑ ከባቢዎች ስንዴን በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ከፍ ያለ ጠቀሜታ ባላቸው እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ ማተኮራችን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስገኙልን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ረሀብን ዜሮ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን እንደምታደርግ ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተሰሩት ስራዎች ለመጪው ትውልድ ጥሩ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንስተዋል።

ለዚህም ከአምስት ዓመታት በፊት የተቀረጸውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ለአብነት አንስተዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተሮች እንዲሆኑ መለየታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በግብርና ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ እንዲሁም ብዙ ውሃ የማይወስዱ እንደ ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ገብስ የመሳሰሉት ሰብሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርና ስራችን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት፤ ተስማሚ የአየር ጸባይ እንዲሁም አምራች የሰው ሀይል ያላት በመሆኑ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ በመግለጽ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ምግብና የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎቿ ተደራሽ ለማድረግ እያደረገች ያለውን ጥረት በማየት የበለጠ ለማበረታታት ሽልማቱን በመስጠቱም አመስግነዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የምግብ ሉአላዊነት በማረጋገጥ በኩል ታላቅ ውጤት አስመዝግበዋል“ – የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጀት ዳይሬክተር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የምግብ ሉአላዊነት በማረጋገጥ በኩል ታላቅ ውጤት አስመዝግበዋል ሲሉ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት ያስተላለፉት የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጀት ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነት መረጋገጥ በኩል ታላቅ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ ምርት ረገድ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ በእጥፍ ያደገው የስንዴ ምርት ለዚህ ተጠቃሸ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ እህል ምርት እራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረትም ድርጅታቸው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራ አመራር ሰጪነት በተገኘው የግብርና ምርት እድገት ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ሆነ ለሌላው ዓለም በሞዴልነት ልትጠቀስ እንደምትችል አሳይታለች ብለዋል።

ዘገባው ከተለያዩ ሚዲያዎች የተቀነጫጨበ ነው

Exit mobile version