Site icon ETHIOREVIEW

ይግባኝ ሰሚው እነ መስከረም ይከሰሳሉ አለ

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 27 ግለሰቦች ክሳቸው እንዲቋረጥ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ብይን ሻረ።

ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ከ6 ወራት በፊት በአማራ ክልል ተከስቷል ከተባለው ሁከትና አመጽ ጋር ተያይዞ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን የክስ መዝገብ ተካትተው በሽብር ወንጀል ተከሰው የነበሩና ችሎት ባለመቅረባቸው ምክንያት ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ እነ ምሬ ወዳጆን ጨምሮ 27 ተከሳሾች ክሳቸው እንዲቋረጥ በስር ፍ/ቤት የተሰጠውን ብይን ነው የሻረው።

በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ብይን የሻረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከአምስት ወራት በፊት ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ እና መስከረም አበራን ጨምሮ አጠቃላይ 51 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦ ነበር።

በዚህም ቀርቦ በነበረው ክስ ላይ ተከሳሾቹ ”መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” በሚል የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማ ለማራመድ በማሰብ፣ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን መንግስት በተለያየ ወታደራዊ ስልት እና ስትራቴጅ በመውጋት፣ የአማራን ህዝብ ክብር እና ኩራት በወታደራዊ ኃይል መመለስ፣ የመንግስትን ኃይል በማያዳግም መልኩ መደምሰስ፣ የክልሉን ገዢ ፓርቲ ማስወገድ፣ የሀገሪቱን ማዕከላዊ ስልጣን መቆጣጠር፣ የአማራ ክልል የሚዋሰኑባቸው መንገዶችን መዝጋት፣ ህዝብን ማሸበር እና መንግስትን አስገድዶ ከስልጣን ማውረድ የሚሉ የሽብር ተግባር ድርጊቶችን ፈጽመዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

በተለይም ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ተፈፅሟል ባለው የሽብር ድርጊት እንቅስቃሴ የማህበራዊ አገልግሎት መቋረጡንና አመጽ መነሳቱን ጠቅሶ÷ በዚህ የሽብር ተግባር ደግሞ አጠቃላይ 217 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ 297 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም 1 ቢሊየን 298 ሚሊየን 346 ሺህ 276 ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል በማለት በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ለ/፣ 35 እና 38፤ እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ በተከሳሾቹ ማቅረቡ ተጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሕገመንግስትና በሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ክሱ ከቀረበ በኋላ ክስ ከተመሰረተባቸው አጠቃላይ 51 ተከሳሾች መካከል ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ እና መስከረም አበራን ጨምሮ 23 ተከሳሾች ችሎት ሲቀርቡ፤ ቀሪ 27 ተከሳሾች አልቀረቡም።

ይሁንና ችሎት የቀረቡት 23ቱ ተከሳሾች የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን ተከትሎ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

ቀሪ 27 ተከሳሾች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ተከትሎ ፖሊስ እንዲያቀርባቸው ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

በዚህ ጊዜ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ ሊያገኙ እንደሚገባ ጠበቆቻቸው ገልጸው÷ ጉዳያቸው ተነጥሎ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ምሬ ወዳጆን ጨምሮ 27 ተከሳሾችን በሚመለከት የፌደራል ፖሊስ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ ፖሊስ ግን ተከሳሾቹ ጫካ መግባታቸውን ገልጾ ማረጋገጫ ማቅረብ እንደማይችል መልስ ሰጥቶ ነበር።

ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ያልቀረቡ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግና ካልቀረቡ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ጫካ ከሆኑ የጋዜጣ ጥሪ ቢደረግም ተደራሽ ሊሆን አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ የጋዜጣ ጥሪ ማድረግ ሳያስፈልግ ክሱ ይቋረጥ በማለት ብይን ሰጥቶ ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ‘ክስ ይቋረጥ’ ብይንን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ብሏል።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱም የግራ ቀኝ የመልስ መልስና ክርክሮችን መርምሯል።

በዛሬው ቀጠሮም ክሳቸው ይቋረጥ ተብሎ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ሥነ ስርዓታዊ አይደለም በማለት ብይኑን ሽሮታል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version