Site icon ETHIOREVIEW

የትግራይ ኢንደስትሪ ቢሮ 217 ኢንዱስትሪዎች ስራ መጀመራቸውን አመነ ወይስ ካደ?

በትግራይ ክልል ” ከ217 በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረዋል ” ያሉት የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ፓርላማ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት ” ከእውነት የራቀ ነው ” አሉ መባሉ ” ቢሮው አመነ ወይስ ካደ?” የሚል ጥያቄ አስነሳ።
አሃዱና ቲክቫህ በቅብብሎሽ አንዱ ሌላውን ዋቢ አድርገው ባሰራጩት ዜና መግቢያና ርዕስ ቀዳሚ ያደረጉት “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት ከዕውነት የራቀ ነው” በሚል ነው። ዜናው በመሪ ርዕሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የቀረበውን ክስ አላብራራም፣ እሳቸው ካሉት ጋርም አላነጻጸረም። ይልቁኑም 217 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ስራ መጀመራቸውን ይመሰክራል።
የትግራይ ኢንዱስትሪ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረሚካኤል ” በአሁኑ ወቅት በክልሉ ስራ የጀመሩት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ ሁለት መቶ አነስተኛ ፣ አምስት መካከለኛ እንዲሁም አስራ ሁለት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ” ሲል ዜናው በትምህርተ ጥቅስ የተጠቀሰውን አንቀጽ ማስፈሩን ያዩ ለዝግጅት ክፍላችን ” ሚዲያዎቹ ዜና አያነቡም፣ ወይም አይረዱም፣ አለያም ሙያዊ ግድፈት አለባቸው” ሲሉ ተችተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እሽቅድድም በሚመስል መልኩ ለላይክና ተከታይ ለማሰባሰብ የሚሰሩ ዜናዎች በስሙ የሚማልበትን “ጋዜጠኝነት” እያደር ቁልቁል እያወረደው እንደሆነ ያመለከቱ፣ ሜዲያዎቹ ለማስተላለፍ የፍለጉትም አሳብ በዕርጋታ ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል። የተጠቀሱትን የክልሉ የኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ እውነት በመናገራቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ በፓርላማ ሪፖርታቸውና ማብራሪያቸው ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በትግራይ ከሁለት መቶ በላይ አምራች ኢንደስትሪዎች ስራ እንዲጀመሩ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል። ለትግራይ በቀጥታ ከፌደራል መንግስት ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰጠቱን በጠቆሙበት ማብራሪያቸው ከሁለት መቶ በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጋቸውን ከማመልከታቸው ውጭ ዝርዝር ጉዳይ አላነሱም።
በዚሁ የትግራይን ጨምሮ መላው የአገሪቱ ህዝብ እየሰማ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” ወደ ስራ የገቡት ከሁለት መቶ በላይ አምራጭ ኢንዱስትሪዎች አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ታላለቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ጥሬ ዕቃ አርራቢዎች ወዘተ” ብለው ሲያስረዱ አልተሰሙም።
መረጃውን የሰጡት ሃላፊ ሳይሆን ሚዲያዎቹ ባልተባለ ጉዳይ ነቀፌታን ማቅረባቸውና ከንቀፊታው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተናገሩትን ንግግር ባልሰማ ማለፋቸው መነሻው ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው ዜና የሚከታተሉ በጽሁፍ “ይገርማል” ሲሉ ልከውልናል። ዜናውን አውዱ እንዲስተካከል አድርጎ መስራቱም ያስፈለገው በዚሁ ጥቆማ መሰረት ነው።

የትግራይ ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ የሰጡት መረጃ ዕውነትነት ያለው በመሆኑ ለሌሎች የክልሉ ቢሮዎችና ሃላፊዎች ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ዜናውን የተመለከቱ ተናግረዋል። አያይዘውም ዜናውን በቅብብሎሽ የዘገቡት ሚዲያዎች እርስ በርስ የሚጣላ ዜና ከመስራት ራሳቸውን ቢያርቁና ከአደባባይ ስህተት ራሳቸውን እንዲጠብቁ መክረዋል።
ሚዲያዎቹ በዘገባቸው ማገባደጃ “ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረው ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለው ነበር ” የሚል ሃረግ ከተው ከላይ በርዕስ የተነሱበት የውግዘት ዜና በራሳቸው አምክነውታል። ዜናውን ጠልቀው ሳያነቡ በማህበራዊ ገጾች የሚራቡ በሚበዙበት አገር መረጃው ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስከትል ከወዲሁ መገንዘብ እንደሚገባ ተመልክቷል።

“ይሁን እንጂ” ይላል ዘገባው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ካስታወሰ በሁዋላ፣ “ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ፤ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ሪፖርት በተጨባጭ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የተራራቀ ነው ሲል ሪፖርቱን ውድቅ አድርጓል” ሲል ዳግም ከራሱ ጋር ይጣላል። ሪፖርቱ ከራሱ ጋር አንቀጽ በአንቀጽ ከመላተም አልፎ ” መሬት ላይ ካለው ዕውነት ጋር የተራራቀ ነው” ሲል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳሳተ ሪፖርት ስለማቅረቡ በንፅፅር አላሳየም።
አቶ መላኩ የሚመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቀረበ የተባለው የተሳሳተ ሪፖርት በዜናው ጭራሽ አልተካተተም። ወይም ሃላፊው እንዲዘረዝሩና የስህተተ መረጃ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመቅረቡ በዋቢነት የተቀመጠ አንዳችም አመልካች ሃረግ አልተካተተም። ይህ በሆነበት “ሃሰተኛ” ተብሎ የተፈረበት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ለመጠየቅና መረጃውን ምሉዕ ለማድረግ ስለመሞከሩም የተባለ ነገር የለም።
“የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረሚካኤል በአሁኑ ወቅት በክልሉ ስራ የጀመሩት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ 2 መቶ አነስተኛ ፣ 5 መካከለኛ እንዲሁም 12 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ” ብለዋል። ሲል ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በትግራይ ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ከሁለት መቶ በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ዝርዝር ሳያቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለተናገሩት ማረጋጋጨ የሰጠ ሆኗል። ዜናው 217 የተለያዩ ደረጃ ያሉዋቸው ኢንዱስትሪዎች ስራ መጀመራቸውን ሃላፊው አምነው ምስክር እንደሰጡ ምስክር ሆኖ የሚመዘገብ ሆኗል።
ዜናው ከላይ ከዘገበው ጋር ዳግም ሲላተም ” ነገር ግን ” ብሎ የጀምራል።” ነገር ግን ሁለት መቶ አስራ ሰባት ኢንዱስትሪዎች ሁለገብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስራ ጀምረዋል ተብሎ የተገለጸው ከእውነታው ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል” ሲል ሃላፊውን እንዳሻው ያላጋቸዋል።
“ከፍተኛ የብድር እና የወለድ መጠንን ጨምሮ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር አሁንም ግዙፍ  ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዳይጀምሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ በቀጠለበት አግባብ ሁለገብ ድጋፍ ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም ሲሉ ተችተዋል” የሚለው ዘገባ የድጋፍና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመላው አገሪቱ የሚታይ እንደሆነ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የሚያስታውቀውና ችግር መሆኑን አንስቶ ተቺውን ስለመጠይቁ የተባለ ነገር የለም።
ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ በተጣለ ማዕቀብ፣ የኢኮኖሚ ሸርና ሽፍትነት፣ የብድር መቆምና የዓለም ወቅታዊ ቁመና እንደ ምክንያት ተጠቅሶ በፓርላማ መቀረቡን ሃላፊው አስታውሶ ዜናውን ለማመጣጠን ስንዝር ያልተራመደው አሃዱ ሚዲያ፣ “ከ37 ቢሊዮን ብሩ ስንት ደረሳችሁ? ስንቱን ተጠቀማችሁበት” ብሎ ቢያንስ ለማዳመቂያ እንኳን ስለመጠየቁ በዜናው አልተመለከተም።
“በክልሉ በነበረው ግጭት የተነሳ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከነበረበት ከፍተኛ ጉዳት በዘላቂነት እንዲያገግም መሬት የወረዱና ተጨባጭ ድጋፎች እንዲደረጉም ነው የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሪ ጥሪ ያቀረቡት ” በሚል የተቋጨው ዜና ከቲክቫህ “ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የአሀዱ ነው” ሲል ምስጋና በመስጠት ነው።
ዜናውን ከአስተያየት ጋር በካሜራ አንስተው የላኩልን ” ሃላፊው ሃቀኛ ናቸው። ሌሎችም እሳቸውን መምስለ አለባቸው። ለዚህ ተግባራቸው በአደባባይ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ዜና ሳታነቡ ርዕስ አይታችሁ የምታጋሩም ተማሩበት” ብለዋል።

ከጎልጉል የተወሰደ

Exit mobile version