Site icon ETHIOREVIEW

ጌታቸው ረዳ ሁለት ተቃራኒ ምስክርነት ሰጡ “ከመንግስት ጋር ተስማምተናል፣ ጥርጣሬ አለ”

“በአከባቢያችን ያለው ፓለቲካዊ ሁኔታ እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ እንደ አገር የውስጥ ሰላማችን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ ከፌደራል መንግስት ጋር መግባባት  ተደርሷል” ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ መናገራቸው ተሰማ። ይህን ባሉበት አንደበታቸው በሁለታችን መካከል ጥርጥር መኖሩን አስታወቁ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ለክልሉ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ መግለጫቸው ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ ነው ከመንግስት ጋር መስማማታቸውን ያስታወቁት።

ትህነግ ዳግም ለመዋጋት ዝግጅቱን ጨርሷል በሚል ውጊያ በቅርቡ እንደሚጀመር ሲጠብቁ ለነበሩ የአቶ ጌታቸው መግለጫ አስደንጋጭ ሆኗል። የውጊያን ሳይሆን የጥንቃቄንና ሰላም አስፈለጊነትን አንስተው በጋር ለመስራት መስማማታቸውን መናገራቸው “ውጊያ ይቀሰቀሳል” በሚል ስጋት ለገባቸው ወገኖች ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ የሚሰጥ ሆኗል።

“ለፌደራል መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበናል” ማለታቸውን የገለጸው ቲክቫህ የሪፖርታቸውን ይዘትና ግብረ ምላሽ ስለማብራራታቸው አልጻፈም። ይሁን እንጂ አቶ ጌታቸው ክልሉን በወጉ መምራት እንዳልቻሉ ተገልጾ ትችት ገጥሟቸዋል።

አዲስ አበባ በሚኒሊክ ሙዚየም ምረቃ ስነስርዓት ላይ የታደሙት አቶ ጌታቸው ወደ መቀለ ተመልሰው በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደወትሮው ክርክር የሚያስነሳና ለሌላ ምልሻ የሚጋብዝ ወሬ አላወሩም።

የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በአንድነት ከፌደራል መንግስት ጋር በአዲስ አበባ ስለተካሄደው ውይይትና ውጤት እንዲያብራሩ ጥያቄዎች ተሰንዝሮላቸዋል።

ወልቃይት ካልተመለሰ በአገሪቱም በሁሉም አካባቢ ሆነ በትግራይ ሰላም በማስከበር ሂደት ተሳታፊ እንደማይሆኑ አስታውቀው የነበሩት የትግራይ አስተዳዳሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘንድ ቀርበው ስለተደረገው ግምገማ አቶ ጌታቸው ” ለፌደራል መንግስት የስራ አፈፃፀም ሪፓርት አቅርበናል። በአከባቢያችን ያለው ፓለቲካዊ ሁኔታ እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ እንደ አገር የውስጥ ሰላማችን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ ከፌደራል መንግስት ጋር መግባባት  ተደርሷል ” የሚል ጥቅል ምላሽ ሰጥተዋል።

“የኤርትራ ወራሪ ሰራዊት 53 የትግራይ ክልል ወረዳዎችን በሃይል ይዟል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ደጋግመው መናገራቸው አይዘነጋም። “በአካባቢያችን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ጥንቃቄ ስለሚሻው” ሲሉ የገለጹት ስምምነት ከኤርትራ ጋር ስለመያያዙ ግን ፍንጭ አልሰጡም። እሳቸው ፍንጭ ባይሰጡም የኤርትራ መንግስት እጁን ከኢትዮጵያ ላይ የማይሰበስብ ከሆነ ግን በሃይል ለመገርሰስ መንግስት ዕቅድ እንዳለው በስፋት ስለሚነገር፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከገነባቸው ሁሉ አቀፍ መከላካያ ጥንካሬና ዘመናዊነት ጋር በተያያዘ ከሻዕቢያ ዘንድ ፍርሃቻ መኖሩ በተለያዩ አግባቦች እየተገለጸ ነው።

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ተለጉመው የኖሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋፍ ማዕቀቡ ከተነሳላቸው በሁዋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአፍሪካ ቀንድ ፊት አውራሪ ለመሆን መታየት አብዝተው ነበር። በተለይ ከመቋዲሾው መንግስት ጋር አብረው ኢትዮጵያን ሊያጠቁ እንደሚችሉም አመልክተው ነበር።

ከጣሊያኑ የአፍሪካ አገሮች ስብሰባ ጀምሮ ዝምታን የመረጡት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በህግ እስከሚወሰን ድረስ ከያዙት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ሊሰጣቸው እንደሆነ አቶ ጌታቸው ባይናገሩም ኢትዮ12 ሰምታለች።

በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረውና የሻዕቢያ እጅ ያለበት ግጭት መልክ እየያዘ እንደመጣ አንዳንድ ምስክሮች እየገለጹ ባለበት ሁኔታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስት ጋር መስማማቱን ማስታወቁ ለሻዕቢያ ይበልጥ ስጋት እንደሚሆንበት ሁኔታውን የሚከታተሉ ይናገራሉ።

ከፌደራል መንግስት በተካሄደው ውይይት “በሃይል የተያዙ የምዕራብ ዞን ” ሲሉ በጥቅሉ የገለጿቸው አካባቢዎች አሁን ባለው ሁኔታ ሪፈረንደም ሊካሄድባቸው እንደማይችል አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰፋሪዎች መስፈራቸውንና ፤ የአካባቢውን ዴሞግራፊ ለመቀየር እንቅስቃሴ ስላለ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ሳይመለሱ ሪፈረንደም ማድረግ እንደማይቻል አብራተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደሮችም ” ሪፈረንደም የሚባል ነገር አናውቅም። አልሰማንም ሲሉ ለዲደብሊው መናገራቸው ይታወሳል። ከሁለቱም ወገን አማራጭ ህዝበ ውሳኔ የመቀበል አዝማሚያ አለመታየቱ መንግስትን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እንደተገለጸው አወዛጋቢዎቹን ስፍራዎች በአንድነት ልዩ ክልል በማድረግ ከትግራይና አማራ ክልል ነጻ የማድረግ አካሄድ ሊሞከር እንደሚችል ግምት እየተሰጠ ነው።

ይህ አዲስ ክልል የመፍጠር አሳብ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን፣ በልዩ ልዩ መድረኮች፣ በፓናል ውይይትና በህዝባዊ ስብሰባዎች ለመንግስት እንደ ግብዓት ሲቀርብ የነበረ አሳብ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በሚቀጥለው ወር መጋቢት የአፍሪካ ህብረት ፣ የተባበሩት መንግስታትና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በተገኙት የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ለውይይቱ ስኬት የበኩሉ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም አመልክተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ህወሓት መልሶ እንደ ፓለቲካ ፓርቲ የመመዝገብ ጉዳይ የሚመለከት ጥያቄም ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም፤ ከህወሓት የፓለቲካ ፓርቲነት ምዝገባ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ መሰረት ያለው የህግ ክፍተት እንዲስተካከል ጉዳዩ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መላኩን ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው ይፋ ባይናገሩም ስለ ምርጫ ጉዳይ መንግስት አጥብቆ መመሪያ መስጠቱ ተሰምቷል። በቀጣይ ምርጫ ሁሉም የክልሉና የፊደራል የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሳተፉበት አግባብ ስላለ ትህነግ ሌሎች አማራጮች እንደቀረቡለት ተሰምቷል። ይሁን እንጂ ዝርዝሩ በአቶ ጌታቸውም ሆነ በሌሎች አካላት ለጊዜው ይፋ አልሆነም።

አቶ ጌታቸው በመንግስትና በትህነግ መካከል ጥርጣሬና አለመተማመን እንዳለ አስታውቀዋል። ስምምነት መደረሱን በጠቀሱበት መግለጫ ላይ ጥርጣሬ መኖሩን ሲገልጹ ያነሱት የታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት ጉዳይ ነው።

መንግስት ከሚልከው በጀት እየቀነሱ 270 ሺህ ታጣቂዎችን እንደሚቀልቡ አስቀድመው ያስታወቁት አቶ ጌታቸው ይህን ሃይል አሁን ላይ መበተን እንደማይፈልጉ ሲገልጹ ” ባለውለታ ነው” በሚል ሲሆን፣ የሚበተነው ቅድሚያ ከፌደራል መንግስት በኩል የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መተግበር እንደሚገባው ካስቀመጡ በሁዋላ ነው።

መንግስትም ትህነግም ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆናቸውን ቢናገሩም፣ በወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ስምምነት ዓመት ከስድስት ወር ባለበት ደረጃ መቀጠሉ ቀጣይ ስጋት አስነስቷል።

Exit mobile version