ፈቃድ ሳይኖራቸው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አማረ እና ቤተሰቦቹ በተባለ ህንፃ ላይ ቢሮ ተከራይተው ሃሰተኛና የፈጠራ ወሬ ሲያሰራጩ ነበሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገለጸ። ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በህዝብ ጥቆማ እንደሆነ ተመልክቷል።
ሐሰተኛ እና አፀያፊ የፈጠራ ታሪክ እያሰራጩ ህዝብን የሚያደናግሩ ዩቲዩበሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ ሲያስታውቅ አንድ ተጠርጣሪ ብቻ ስምንት የዩቲዩብ ቻናል ተከፍቶ ተገኝቷል። ፖሊስ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሃሰተኛ መረጃ ለመስጠት በቢሮ የነበሩ ሰዎችን ማግኘቱንም አስታውቋል።
ሃሰተኛ መረጃ እና ከማህበረሰቡ መልካም ባህልና ወግ የተቃረኑ አፀያፊ የፈጠራ ታሪኮችን በማህበራዊ ሚዲያ እያሰራጩ በህዝብ ላይ ውዥንብር እና መደናገርን የሚፈጥሩ ግለሰቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ ከመጠቀም ይልቅ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ከእውነት የራቁ መሰረተ ቢስ የፈጠራ አፀያፊ ወሬዎችን እየፈበረኩ በማሰራጨት የህዝብን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ዩቲዩበሮችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 አማረ እና ቤተሰቦቹ በተባለ ህንፃ ላይ ቢሮ ተከራይተው የተለያዩ የዩቲዩብ ገፆችን በመክፈት የማህበረሰቡን ሥነ ልቦና የሚጎዱ የፈጠራ ታሪክ በማሰራጨት የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በህዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተይዘው በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል መቅደስ መብራት መኮንን የተባለችው ግለሰብ ሮሄ፣ ልዩነት፣ ጣዕም፣ አዲስ አለም፣ ዘይቤ፣ ህይወት፣ እይታ፣ እና ዩኒት ህይወት የተባሉ የዩቲዩብ ገፆችን በመክፈት በስራ አስኪያጅነት ስትመራ የነበረች ናት ተብሏል፡፡
ብሩክ ወርቅነህ ጌታሰው የተባለ ግለሰብ ደግሞ ገፆቹን በምክትል ስራ አስኪያጅነት እና በአስተባባሪነት ሲመራ የነበረ ሲሆን ናትናኤል አበራ በቀለ፣ እየሩሳሌም አስማረ ምህረት እና ምህረት ያሲን ቲጋ የተባሉት ግለሰቦች ደግሞ በፕሮግራም አቅራቢነት እንዲሁም ናትናኤል ዮሃንስ አሸነፍ በካሜራ ባለሙያነት ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ስምንት የዩቲዩብ ገፆች በተጨማሪ ክህሎት እና ሲንግል የተባሉ ሌሎች ሁለት የዩቲዩብ ገፆችም በዚያው ህንፃ ላይ የፈጠራ ወሬ ሲፈበርኩ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ተከራይተው በሚሰሩበት ህንፃ 8ኛ እና 13ኛ ፎቅ በሚገኘው ቢሮአቸው ላይ በህግ አግባብ ባደረገው ብርበራ የፈጠራ ወሬ ለመቅረፅ እና ለማሰራጨት የሚጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ተይዘዋል፡፡
ግለሰቦቹ መረጃውን ለማሰራጨት የሚያስችል ከሚመለከተው አካል የተሰጠ የህጋዊነት ማረጋገጫም ሆነ ፈቃድ እንደሌላቸው በምርመራው ሂደት መረጋገጡንም ከየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሃሰተኛ እና የፈጠራ ወሬዎቹን የሚሰራጩት ታሪኩን ለሚተውኑላቸው ግለሰቦች ገንዘብ በመክፈል ሲሆን በወቅቱ ጉዳዩን በጥልቀት ሳይረዱ እና መረጃው ሳይኖራቸው የማያውቁትን የፈጠራ ታሪክ ሊሰሩ ለቀረፃ ስራ የተጠሩ ሌሎች ሶስት ሰዎችን ፖሊስ አግኝቷል፡፡
መሰል የውሽት ታሪኮችን ቀልብ በሚስብ መልኩ እያቀናበሩ በማሰራጨት በህብረተሰቡ ላይ መደናገርን የሚፈጥሩ ሌሎች ግለሰቦችም ተለይተው የታወቁ እና በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትል ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት ከባህልም ከስነ ምግባርም ያፈነገጡ የፈጠራ ወሬዎችን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ በሚመለከትበት ወቅት ገፆቹን ከመከተል እንዲቆጠብ እና የሌሎች መረጃዎችንም ትክክለኛነት በማረጋገጥ ራሱን ከአላስፈላጊ መደናገር እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡