Site icon ETHIO12.COM

የሩስያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬን በኩል የማጥቃት ዘመቻቸውን ማፋፋማቸው ተነገረ

የሩስያ ኃይሎች በምሥራቃዊ ዩክሬን በኩል የሚያደርጉትን የማጥቃት ዘመቻ እንደገና አጠናክረው መቀጠላቸው ተነገረ።

ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የዘለቀውና 46ኛ ቀኑን የያዘው የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነት በዛሬው ዕለት በዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛት በኩል እየተፋፋመ መምጣቱ እየተዘገበ ነው።

ዩክሬን በምሥራቃዊ ግዛቶቿ በኩል ከሩስያ ኃይሎች የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት ኃይሏን እያሰባሰበችና በአካባቢው የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ከስፍራው የማስወጣት እንቅስቀሴዋን መቀጠሏን የተለያየዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ፥ በዛሬው ዕለት የሩስያ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ምሥራቃዊቱ ከተማ ካርኪቭ እየተተጓዙ መሆናቸውን የሳተላይት ምስሎችና የዩክሬይን ወታደራዊ ምንጮች አረጋግጠዋል።

ከትናንት ወዲያ የሩስያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከካርኪቭ በስተምሥራቅ በኩል ከሩስያ ድንበር አካባቢ በቅርበት ወደምትገኘው ቫልኪ ቡርሉክ ከተማ እየተመሙ እንደነበርም የሳተላይት ምንጮችን ዋቢ አድርገው መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበው ነበር።

በዛሬው ዕለት ደግሞ የሩስያ ኃይሎች ተጨማሪ ተዋጊ ዩኒቶችን ( አሃዱዎችን) በማንቀሳቀስ ካርኪቭ ውስጥ ኢዙም በተሰኘ ቦታ የሚገኘውን የዩክሬይን መከላከያ ኃይል ሰብረው ለመግባት እና ማሪዩፖል ከተማን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየሞከሩ መሆናቸውን ነው የዩክሬይን ወታደራዊ ባለስልጣናት ስለጥቃቱ ባወጡት መግለጫ ያረጋገጡት።
ድርስ ካርኪቭን በከፊል በሩስያ ጦር ስር ለማዋል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ከተማዋ በከባድ መመሳሪያዎች እየተደበደበች መሆኗን ከዩክሬን ጦር ኃይሎች የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ “የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል እያጋጠመን ያለውን ከባድ ጦርነት ለመፋለም ዝግጁ ነን “ እያሉ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በሩስያ ላይ የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ እንዲጣል እየወተወቱ ሲሆን፥ ለአገራቸው ህዝብ ባደረጉት ንግግር “ከእንግዲህ የምንጠብቀው ጊዜ የለም፤ ሩስያ የምትተማመንበት የነዳጅ ገቢ ምንጭ መቆረጥ አለበት” በማለት ማዕቀቡ እንዲፋጠን ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ተማጽነዋል።

በሌላ በኩል የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፥ አገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ እና የፋይናንስ ድጋፍ እንደምታጠናክር ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “ የትግል አጋርነትን ለማሳየት የተደረገ ነው “ ባሉት በዩክሬኗ ዋና ከተማ ኪየቭ ትናንት ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት፥ 120 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችንና አዳዲስ ፀረ-ሚሳኤል መሳሪዎችን ለዩክሬን መንግስት ለመስጠት ተስማምተዋል።

በተመሳሳይ የአውሮፓ ኀብረት የውጭ ጉዳይ ዋና ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ “ ዩክሬን እንደገና ታንሰራራለች፥ ጠንክራም ትወጣለች” ካሉ በኋላ ፥ ለዩክሬናውያንም “ የአውሮፓ ኀብረት በመንገዳችሁ ሁሉ ከጎናችሁ ነው” ብለዋቸዋል።

የሩስያ ኃይሎች በምስራቁ የዩክሬን ግዛት በኩል የጀመሩትን ዘመቻ እያቀጣጠሉ በመጡበትና የሉሃንስክ ክልልን ቀለበት ውስጥ ባስገቡበት በአሁኑ ሰዓት ነዋሪዎቹ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ ተላልፎላቸዋል።

በዚህም መሰረት ለነዋሪቹ መጓጓዣ በርካታ ባቡሮች ተመድበውላቸው ከተማዋን ለቅቀው እየወጡ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቅቀው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሩስያ ጦር ዛሬ ማለዳ ላይ ሉሃንስክ እና ዲኒፕሮ በተባሉት የዩክሬን ክልሎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት እንደተፈጸመም ተገልጿል።በዚህም ትምህርት ቤቶችና በርካታ ህንፃዎች መውደማቸው እንዲሁም የሰው ህይወት ማለፉን ዘጋርዲያን ጋዜጣና ሌሎች የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ለአገራቸው ህዝብ ባደረጉት ንብብር፥ “ይህ ጦርነት ከባድ ቢሆንም በድል እንደምናጠናቅቀው እምነት አለን፤በአንድ በኩል እየተዋጋን፥ በሌላ በኩል ጦርነቱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ዝግጁ ነን “ ብለዋል።

በተመሳሳይ ዩክሬን በኢኮኖሚ ሚኒስትሯ ዩሊያ ስቪሪደንኮ በኩል ዛሬ እንዳስታወቀችው፥ ለሩስያ በዓመት 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ የሚገመተውን ከሩስያ የምታስገባውን የሸቀጦች ንግድ ሙሉ በሙሉ አግዳለች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ኢሪያና ቬሬስቹክ በበኩላቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፥ አገራቸው ሰላማዊ ዜጎች የጦርነት አካባቢዎችን ለቅቀው የሚወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዘጠኝ የሰብዓዊ አቅርቦት መተላለፊያ መንገዶችን ከፍት ለማድረግ መስማማቷን አስታውቀዋል።

የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተደጋጋሚ እንዳስታወቁት፥ “የዩክሬን መንግስት በሩስያውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ ከማድረግና ዓለምአቀፍ ህግን በመጣስ የምዕራባውያን ተላላኪ በመሆን የአገሬን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ከሚጥል ድርጊቷ ካልተቆጠበች በስተቀር ዘላቂ ሰላም ሊመጣ ፥ ውጊያውም ሊቆም አይችልም” የሚል አቋም ነው ያላቸው።

በሌላ በኩል የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ” ሩስያ በቀጣይ ልታደርግ የምትችለውን ወታደራቂ ጥቃት ለመከላከል ያስችለኛል” የሚለውን በዩክሬን ድንበር ላይ ያለውን ወታደራዊ ይዞታ የማጠናከር ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

የኔቶ ዋና ጸኃፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ ከቴሌግራፍ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፥ “የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለፈጸሙት ድርጊት የረዥም ጊዜ ዋጋቸውን ሊያገኙ በሚችሉበት መሰረታዊ የሽግግር ጊዜ ላይ ነን፥ ለዚህም ወታደረዊ ኮማንደሮቻችን አማራጮችን እንዲያቀርቡልን ጠይቀናቸዋል“ ብለዋል።

ይህ የወታደራዊው ሹም ንግግር ምን ማለት እንደሆነና የክሬንና ሩስያ ጦርነት ወዴት እንደሚያመራ አሁንም እያነጋገረ ይገኛል።
Fbc

Exit mobile version