Site icon ETHIO12.COM

የ2015 በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ስራ ማከናወን

የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ስራ ለማከናወን በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን ተገለጸ

የፌዴራል መንግስት የ2015 በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ስራ ለማከናወን በሚያስችል ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማዕቀፍ በመመራት እየተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ገለጹ፡፡

የ2015 በጀት በጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማእቀፍና የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ባገናዘበ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የ2015 በጀት አመት የበጀት ዝግጅትን አስመለክተው እንደገለጹት 170 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት የ2015 በጀታቸውን ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ አቅርበዋል።

የበጀት ዝግጅቱ ስትራቴጂያዊ ለሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝምና ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር እዮብ ጠቁመው፣ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ከመደበኛ በጀት ላይ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ቅናሽ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡

የበጀት ጉድለትን በተመለከተም ከውጭ የሚገኘው ሀብት በታሰበው መጠን ላይገኝ ስለሚችል መንግስት ከሀገር ውስጥ ከሚመነጨው ሀብት ማለትም ከግምጃ ቤት ሰነድና ከሌሎች የሀገር ውስጥ ምንጮች ለሟሟላት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉ አበራታች ውጤት በመገኘቱ የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባበስ ሁኔታ ለማሟለት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያ አማካይኝነት ውጤት በመገኘቱ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እንዳገዘም ገልጸዋል፡፡

በ2015 በጀት አመት አዳዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደማይደረጉ ዶ/ር እዮብ ጠቅሰው፤ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የካፒታል ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወጪ በትጋት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እንዲቻል የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2015 በጀታቸውን ባስገመገሙበት ወቅት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል::

ከሚያዚያ 25/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በተካሄደው የበጀት ስሚ መርሀ ግብር ላይ ከጥቂት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በስተቀር አብዛኞቹ መስሪያ ቤቶች በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ በላይ ማቅረባቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው ከያንዳንዱ ባለበጀት መስሪያ ቤት ጋር በተደረገው ውይይት በጀታቸውን በተሰጠው የበጀት ጣሪያ መሰረት አስተካክለው እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ መደረሱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የ2015 የፌዴራል መንግስቱ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ከሀምሌ 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። via OBN

Exit mobile version