Site icon ETHIO12.COM

ብርሃኑ ባይህ እና አዲስ ተድላ ምህረት ሊደረግላቸው ይችላል ተባለ

ሠላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በጥገኝነት የሚገኙት ሁለት የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቀጣይ ቀናት ይቅርታ ሊደረግላቸው ይችላል ተባለ።

እነዚህ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ላለፉት ሦሰት አስርት ዓመታት ቆይተዋል።

የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን ከመያዙ አንድ ቀን ቀደም ብለው በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ከተጠለሉት አራት የወቅቱ ከፍተኛ ባለስልጣንት መካከል የነበሩት ብርሃኑ ባይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ሌፍተናንት ጀነራል አዲስ ተድላ የሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ነበሩ።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩት ሁለቱ የቀድሞ ባለስልጣናት፤ የሞት ፍርዳቸው ወደ እድሜ ልክ እስራት በርዕሰ ብሔሯ ተቀንሶላቸዋል።

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በደርግ መንግሥት ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ የተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው ነው የሞት ቅጣት የተበየነባቸው።

አቶ አወል እንዳሉት የጣሊያን ኤምባሲ ሁለቱ ግለሰቦች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ለበርካታ ዓመታት በመቆየታቸው እና እድሜያቸው መግፋቱን ተከትሎ ከእድሜ ጋር ተያይዘው በሚመጡ ሕመሞችም ችግር ላያ ያሉ መሆኑን በመጥቀስ ግለሰቦቹ ነጻ እንዲወጡ ሃሳብ መቅረቡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እኛ ያሉበትን ሁኔታ አናውቅም። የሚታመሙ ሰዎች መሆናቸውን ከኤምባሲው ተገልጾልናል። ኤምባሲው ግለሰቦቹ ቢወጡ የሚል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል” ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግም በተመሳሳይ የተላለፈባቸው የሞት ፍርድ ወደ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀነስ በይቅርታ እና የምህርት ቦርድ በኩል ለርዕሰ ብሔሯ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል።

“ግለሰቦቹ ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል በይቅርታ የሚያስለቅቅ ባይሆንም፤ ግለሰቦቹ ባለፉት 30 ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እስር በሚመስል ሁኔታ ነጻነታቸውን አጥተው ቆይተዋል” ብለዋል።

የጣሊያን ኤምባሲ ለዐቃቤ ሕግ ባስታወቀው መሠረት ግለሰቦቹ ከኤምባሲው ምንም አይነት ድጋፍ ሲደረግላቸው አልነበረም። ከቤተሰባቸው ይቀርብላቸው የነበረውን ቀለብ እየተጠቀሙ ነው እስካሁን የቆዩት ብለዋል አቶ አወል።

በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሠረት ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የሞት ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀነስ ካደረጉ በኋላ በቀጣይም ዐቃቤ ሕግ ግለሰቦቹ በአመክሮ እንዲለቀቁ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ አቶ አወል አስታውቀዋል።

“ፕሬዝደንቷ የሞት ቅጣቱን ወደ የእድሜ ልክ ቅጣት ቀይረውታል። በቀጣይ ግለሰቦቹ እስካሁን የቆዩበት ሁኔታ ከጥፋታቸው እንዲማሩ ስላደረጋቸው እና ከዚህ በኋላ ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ማደረግ የፍትሕ ዓላማ ስላማይሆን ሊወጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ከሕግ አግባብ ነገሮችን ለማየት ጥረት አድርገናል። በዚህ መሠረትም ሰዎቹ በአመክሮ እንዲላቀቁ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ዛሬ ወይም ሰኞ እንልካለን” ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ደግሞ ይህን ከመረመረ በኋላ ግለሰቦቹ በቀጣይ ቀናት በአመክሮን እንዲለቀቁ ያጸድቃል ብለን እናስባለን ሲሉ አቶ አወል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የግለሰቦቹን ጉዳይ የሚመለከተው በተከሰሱበት ወንጀል ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ ብሎ በፈረደባቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኤርትራ ነጻነት ግንባር አሥመራን ሲቆጣጠርና የኢህአዴግ ኃይሎች ድል እየቀናቸው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት አንድ ሳምንት ሲቀራቸው የወቀቱ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ስልጣናቸውንና አገራቸውን ለቀው አስካሁን ድረስ በጥገኝነት ወደሚገኙባት ዚምባብዌ ካቀኑ ከሳምንት በኋላ ነበር ባለስልጣናቱ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ የገቡት።

ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንዲሁም ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ በውቅቱ ተይዘው ከነበሩ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በስልጣን ዘመናቸው ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው በሌሉበት የሞት ቅጣት ተወስኖባቸው ነበር።

መንግሥትም የጣሊያን መንግሥት ተፈላጊዎቹን አሳልፎ እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ጣሊያን ጥያቄውን ሳትቀበለው ግለሰቦቹን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲዋ ውስጥ አስጠግታ 30 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ለቀሩት ጊዜ ጠብቃ አቆይታቸዋለች።

በወቅቱ በኤምባሲው ውስጥ ጥገኝነት በመጠየቅ ገብተው የነበሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት ስምንት የነበሩ ሲሆን አራቱ በእራሳቸው ፈቃድ ኤምባሲውን ለቀው መውጣታቸው ይነገራል።

አሁን ኤምባሲው ውስጥ ከሚገኙት ከኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጀነራል አዲስ ተድላ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም አገር ለቀው ሲሄዱ ለቀናት የመሪነት ቦታውን ይዘው የነበሩት ሌ/ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይሉ ይመኑ ይገኙ ነበር።

እነዚህ ከፍተኛ የቀድሞ ባለስልጣናት በኤምባሲው ውስጥ ጥገኝነት አግኝተው ለተለያዩ ጊዜያት ከቆዩ በኋላ እዚያው እንዳሉ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወቃል።

ዚምባብዌ የሚገኙትንና በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በወቅቱ እጃቸውን ሰጥተው በነበሩ የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ በስልጣን ዘመናቸው ተፈጽመዋል በተባሉ ጥፋቶች የከባድ ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደቱ ለዓመታት ከተካሄደ በኋላ አብዛኞቹ የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ነገር ግን በእስር ላይ ሳሉ ህይወታቸው ካለፈው ውጪ ያሉት ባለስልጣናት ከ20 ዓመታት እስር በኋላ በምህረት ነጻ መውጣታቸው ይታወቃል።

BBC AMHARIC

Exit mobile version