ETHIO12.COM

የትግራይ ረሃብ ድሮም ተደብቆ የኖረ ወይስ አዲስ በሁለት ወር የተፈጠረ? ገለልተኛ ፈራጅ ያታው አወዛጋቢው አጀንዳ! – ሪፖርት

በትግራይ ህዝብ ላይ የሚጮሁ፣ ለትግራይ ሕዝብ እንጮሃለን የሚሉ፣ ለማን እንደሚጮሁና ምን ብለው እንደሚጮሁ ያልተረዱ የሚመስሉ የሚያሰሙት ድምጽ ዓየሩን ሞልቶታል። የትግራይ አክቲቪስት እንደሆኑና ህወሃትን ከሞት አለምልመው ለማስነሳት የሚተጉ ጦርነቱ ” በድል አድራጊው” የትህነግ ሰራዊት እየተቀጣጠለ እንደሆነ ይሰብካሉ። መስማት የቻለው የትግራይ ሕዝብና መላው የአገሪቱ ዜጎች ከሁሉም አቅጣጫ የሚወጣውን ድምጽ እየሰሙ ነው።

መፈናቀሉን፣ ስደቱንና ረሃቡን ወደ ፈለጉት ዓላማ እየጎተቱ መንግስት ላይ ዘመቻ የሚያካሂዱ፣ በመንግስት ላይ ቁጣ እንዲነድ የሚሰሩና ጉዳዩን ለሚከተሉት የፖለቲካ አጀንዳ ማቀጣጠያ ዘይት ለማድረግ መረጃዎችን በማግዘፍና በማጋነን የተበላሸ ስዕል የሚያራቡ ያሉትን ያህል፣ በጨዋነት ችግሩን በመጠቆም ህዝብ እንዲረዳ የሚጠይቁ አልታጡም። ወይም የሚወተውቱ አሉ።

ከትግራይ የሚወጡ ማናቸውም መረጃዎች በሚፈለገው መልኩ እየተቸረቸሩበመሆኑ ቀና ዜጎች ግራ መጋባታቸውን እየገለጹ ነው። ትግራይ ገብተው መውጣታቸውን ከሚናገሩት የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ጀምሮ እስከ ውጭ አገር ያሉት ዋናውን የግጭቱን ስር፣ የሞት፣ የመሰረት ልማት ውድመት፣ መፈናቀልና ስደት፣ እንዲሁም ረሃብ የመሳሰሉትን ጉዳዮች እያንሸዋረሩ ስለሚያቀርቡ ችግሩ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ለማመን ይከብዳል። ከሁሉም በላይ ችግሩ የሚቀሰርባቸው ወገኖች እርግጥ የችግሩ ሁሉ ባለቤት ናቸው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መመልስ የማይቻለውም ለዚሁ ነው።

የትህነግ ውስን የበላይ አመራሮች መርጠውታል በሚባለው መንገድ፣ ወይም በደጋፊዎቻቸውና በራሳቸው በአመራሮቹ ” የህልውና ጉዳይ” የሚባለው የግጭት አጀንዳ ዛሬ ላይ የወረዛና ጣዕም አልባ በመሆኑ ለክርክር ባይበቃም አንድ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ተክሏል። ይህን አጀንዳ አጽድቶና ከስሩ ጠርጎ የሚያሳይ ሙያተኛ ከስፍራው ማግኘት አልተቻለም።

የሚዲያና የጋዜጠኞች ያለህ !! ሕዝብ ክቡር ነውና

በማይክድራ ከተካሄደው ጭፍጨፋ ጀመሮ ጦርነቱ ተጀምሮ ዛሬ እደረሰበት ደረጃ እስኪደርስ ከስካርና ከወገንተኛነት የጸዳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከንዴትና ከሽንፈት ቁጭት ያላመለጠ፣ የተቀረው ደግም በትህነግ ላይ ካለው የከረመ ጥላቻ ጋር ተያይዞ ከሚያስጮኸው በቀር ገለልተኛ ሆኖ መረጃ የሰጠ መገናኛ አለ ቢባል ራስን ማታለል ነው። ካለም እዛና እዚህ የተባሉትን የሚገጣጥም የወጌሻነት ሪፖርት ቢጤ ካልሆነ በቀር ወደ ፕሮፌሽናል ዘገባ የሚጠጋ ሊሆን የማይችል ነው።

ሙሉ በሙሉ እስኪባል ደረስ የዚህን ሪፖርት አቅራቢም ጨምሮ በስራቸው የጸዱ አይደሉም። ዛሬ በአገራችን የሚታየው የሙያው መልኮስኮስና ዝም ብሎ ማንም እየተነሳ የሚጋለብበት የሱቅ በደረቴ ገበያ አይነት መሆኑ አሳዛኝ ሆኗል። ሰውም ምርጫ አልባ፣ የተጫነውን ሁሉ ሳይመረምር የሚሸከምና የሚያሰራጭ በመሆኑ ችግሩን በእንቅርት ላይ እንዲሉ አድርጎታል። እንደ አገር ሚዲያው በተከፈተለት የመስራት ነጻነት ተጠቅሞ አገርና ወገንን ማገዝ እየቻለ የድርሻውን አለመወጣቱ ለሃሰት ነጋዴዎች በር ከፍቷል። ወይም ተባባሪ አግኝተዋል። እናም ሚድያና ” ጋዜጠኛ ” የሕዝብን ስም እንጂ ክብር ሚዛን ወዴት እንዳለ የዘነጋን ይመስላል። ይህ አደገኛ አካሄድ እጅግ ገዝፎ የወጣው ደግሞ አገሪቱ ከምትከተለው የጎሳ አስተሳሰብ ፖለቲካ መሆኑ ችግሩ ገና ቀጣይነት እንዳለው የሚያሳይ ሆኗል። በሌላ አነጋገር ሙያው በጽንፈኞች ተበልቷል። ተጠልፏል ወይም የቀለብ ሰፋሪዎች መጫወቺያ ሆኗል። በነገራችን ላይ ሚዲያዎች ከጥቂቶች በስተቀር እገሌ ከገሌ ሳይባል የአገሪቱን ተስፋዎች በማትነን ታላቅ ሚና እንደነበራቸው የ1997 ምርጫና ጣጣው ልዩ ምስክር ነው። ይህን ካስታወስኩ ወደ መነሻ አሳቤ ለመለስ።

በትግራይ ረሃብ መቼ ገባ? ዛሬ? ወይስ የኖረ ችግር?

ከላይ በጅምላ የተዘረዘሩት ሃሳቦች በሙሉ ሰፊ በመሆናቸው መዘርዘርና ማየት ስለማይቻል መንግስት ” የህግ ማስከበር” የሚለው ዘመቻ ከተጀመረ በሁዋላ ተከሰቱ የተባሉት ችግሮች በሙሉ ድምዳሜያቸው “ረሃብ” ስለሆነ እዚሁ ላይ ትኩረት መስጠቱን መርጫለሁ። መነሻዬ የመንግስት ሃላፊዎችና የፈረሰው የትግራይ አስተዳደር የያዛቸው ዳታዎች ናቸው።

በትግራይ ክልል ትህነግ ብቸኛ መሪ ድርጅት ነበር። በትግራይ ክልል ከረሃብና እርዳታ ጋር በተያያዘ ትህነግ መልካም ስም እንደሌለው አባላቱ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ዛሬ ድረስ ይህንኑ እየገለጹ ነው። በቅርቡ ትግራይን በጉልበት እስከተነጠቀ ድረስ የራሱ ዳታ እንደሚያሳየው በትግራይ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተረጂዎች ነበሩ። እነዚህ በባህር መዝገብ ተመዝግበው ያሉ ተረጂዎች ብዛታቸውን የፌደራሉ አደጋ መከላከል ኮሚሽንም ያውቃቸውዋል።

በዚሁ መረጃ መሰረት 1.1 ሚሊየን የመደበኛ ሲፍቲ ኔት ተጠቃሚዎች፣ 600 ሺህ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ተቀባይ፣ 110 ሺህ የሚሆኑ ከለውጡ በሁዋላ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ወደ ትግራይ የገቡ ተረጂዎች፣ በድምሩ 1.8 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች የትግራይ ክልል ውስጥ ነበሩ። ይህ አሃዝ ” ሰላም ነበርን” በሚባልበት ጊዜ የነበረ ነው።

በዚህን ወቅት ችግሩን ረሃብ፣ ችጋር ወይም ሌላ ስም አውጥቶ የጠራው ይክልሉ፣ የፌደራል ወይም የዓለም መገናኛ የለም። ወይም የተጠቀሰው ቁጥር ሕዝብ በትግራይ በተመሳሳይ እየተረዳ እንዲኖር ስምምነት ያለ ያስመስላል። ይህን መረጃ የሚያጣቅሱ ” እንዴት ዛሬ በሁለት ወር ውስጥ ትግራይ ረሃብ ገብቶ ሰው ገደለ ይባላል? እንዴትስ ውሃ ጥም ሰው ገደል ተብሎ ይዘገባል? ከሆነስ እንዴት መንግስትን ለትችት ያበቃዋል” የሚል አስተያየት እንዲያነሱ መክንያት ሆኗቸዋል።

አቶ አብረሃ ደስታ እና አቶ ምትኩ ካሳ ምን እያሉ ነው ?

ato Abrha
Commissioner mitku

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ የአረና ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ በትናንትናው እለት ለቪኦኤ ሲናገሩ ከሁለት ወረዳዎች አስራ ሶስት ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት እንደቀረበላቸው አስረድተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ ችግሩ ስር የሰደደ ሲሆን በክልሉ 4.5 ሚልዮን ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል። 2.2 የሚሆኑት ደግሞ ምግብ ቢሰጣቸው እንኳ አብስለው የሚበሉት የላቸውም። ማን እንደዘረፋቸው ባይናገሩም “ተዘርፈዋል” ሲሉ ተድምጠዋል። ስኒና ድስት፣ ቦሃቃና ጭልፋ ተዘርፏል እያሉ ነው።

አቶ አብርሃ የህል ችግር እንደሌለ አመልክተዋል። ችግሩ ያለው እህሉን ለማጓጓዝ የሚጠየቁ አሽከረካሪዎች ” መኪናችን ይወስድብናል፣ ለነብሳቸን እንፈራለን” ማለታቸው ነው። በዚህም ምክንያት በአጀባ ለማዳረስ እየተሞከረ ቢሆንም ብዙ አልተሳካም ብለዋል። እያስተረጎመ የሚዘግበው የቪኦኤ ሪፖርተር አጀባው ያልተሳካበትን ምክንያት አልገለጸም። ወይም አልጠየቀም።

የአደጋ መከለከል ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ዩኤንን ጨምሮ ሶስት የዓለም አቀፍ አገራት ያሉበት ምልክከታ በተወሰኑ ቦታዎች ተድርጎ በተወሰደ ዳሰሳ የተረጂዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን እንደሆነ ገልጸዋል። ከአቶ አብረሃ ጋር በአሃዝ ባይግባቡም ሁለቱም እንዳሉት የእህል ችግር የለም። አቶ ምትኩ እርስ በርስ የማይገናኝ፣ የማይነጋገርና ተመልሶ ተደራጅቶ መንም መፈየድ እንደማይችል የጠቀሱት ” አጥፊው” ሃይል በመበተኑ አልፎ አልፎ እያደፈጠ ጥያት ስለሚተኩስ እርዳታ ማሰራጨቱን አስተጓጉሏል። ያም ሆኖ ግን ለአረጋዊያን፣ ለህጻናት፣ ለመጫቶችና እናቶች መድሃኒትና አልሚ ምግብ በአንቶኖቭ የማድረስ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

92 የማከፋፈያ ጣቢያዎች ተቋቁመው የስብአዊ ድጋፍ የማድረሱ ስራ እየተሰራ መሆኑንን አቶ ምትኩ ገልጸው ” የእጀባ ስራው የተፋጠነ እንዲሆን ከመከላከያ አባላት መካከል የማስተባበሪያ ግብርሃይሉ አባል እንዲሆኑ ተደርጓል” ብለዋል። የሁለቱ ሃላፊዎች መግለጫ በቁጥር ካለው ልዩነት ውጪ በሰጡት ዝርዝር አይጋጭም። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሊቀመንበር ዶክተር ሙሉ መንግስት በሚገባ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንን በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።

ያልተመለሱ ጉዳዮች

ለማሳያ ያህል ይህንን ካልን ላለፉት ሰላሳ አመታት ክልሉን ሲመራ የነበረው ትህነግ እንዴት የስንዴ ተረጂዎችን ማጥፋት አቃተው? ከአፍሪካ አንደኛ የሆነ የንግድ ተቋም የገነባው ትህነግ እርሻው እንኳን ባይሆን እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ እስከመቼ ነበር ስንዴ እየተሰፈረለት እንዲኖር እቅድ የያዘው? ራስን የቻለ መንግስት የመሆን ህልምና፣ ፡ ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን” የሚለው ሩጫ በምን መልኩ ነበር ” ታላቅነትን” ለትግራይ ህዝብ ሊያጎናጽፍ ያሰበው? እስከመቼ ድረስ ነበር ስንዴ እየለመነ በኩራት እየጨፈረ ሊኖር ያሰበው? ይህ የትግራይ ልሂቃን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና እውነት ወዳድ ዜጎች ሊመረመሩትና እውነቱን ሊያስጨብጡ ግድ የሚላቸው የህሊና ፍርድ ጉዳይ ነው?

ጦርነቱ በተጀመረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ የረሃብና የጥማት ዜናው ጎልቶ ሊወጣ የቻለው ለምንድን ነው? በትግራይ እንዴት የውሃ ጉዳጓድ እንኳን መቆፈር አልተቻለም? በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች መቋቋሚያ በህግ የጸደቀ ልዩ በጀት እያላቸው፣ በጀቱን የሚፈቅዱ ባለስልጣናት ራሳቸው ሆነው እንዴት ድፍን ትግራይን ውሃ ይጠማታል? ስንዴው እንኳን ማጓጓዝ አልተቻለም ቢባል መጠነኛ የጉድጓድ ውሃ መቆፈር ያልተቻለበትን ምክንያት መርምሮ የማያጋልጥ ወይም እወነታውን የማያሳውቅ የትግራይ ተወላጅ ባለሙያ በምን መስፍስርትስ ተቆርቋሪ ሆኖ በሕዝብ ስም ይምላል?

የህግ ማስከበር የተባለው ጦርነት በብርሃን ፍጥነት መጠናቀቁን እግር እግር እየተከተሉ ሲዘግቡ የከረሙት ሚዲያዎች፣ ትግራይ ከትሞ የነበረው ኦቢኤን እንዲሆሁም አማራ ማስ ሚዲያ ረሃቡን አስመልክተው ለምን ህዝብ አነጋግረው ግልጽ መረጃ አይሰጡም? ስለምን ሕዝብ እንዲናገር አያደርጉም? ሰው ሞተ የሚባልበት አንዶ ስፍራ አደዋ ከተማ ነው። አደዋ ሄደው ለምን አይዘግቡም? የትህነግ ሚሊሻና ወታደር ቁመና እህል ማዳረስ የማያስችል እንቅፋት የመሆን አቅም ካለው አንድ መፍትሄ እንዲወሰድ ምልከታቸውን በነጻነት ለምን አያቀርቡም?

በውጭም ሆነ በአገር ቤት ያሉ የትህነግ ደጋፊዎችስ ስለምን እህል እንዳይጓጓዝ እንቅፋት መሆንን እንደ ፖለቲካ ድል ወስደው የመደራደሪያ አጀንዳ ያደርጉታል? የትግራይ ሕዝብ እንደተባለው ድሮም ጀምሮ በነበረበት የረሃብ ስጋትና ተረጅነት ምን ያህሉ ሲያልቅ ነው የሚታዘንለት? በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ያቻለል? ወዲህም ተባለ ወዲያ የትግራይ ህዝብ መከራውን እያየ ነው። ድሮም አላማረበትም። አሁንም ያው ነው። ድሮም ርሃብተኛ ዛሬም ያው። የፖለቲካው ቁማር ማብቂያ ያለው አይመስልም።

ማምሻውን ኢዜአ እንደዘገበው በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመቀሌ ቅርንጫፍ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ለ47 ጤና ተቋማት እስከ 18 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የመደበኛና የጤና ፕሮግራም መድሀኒትና የህክምና ግብዓቶችን ማሰራጨቱን ገለጸ፡፡

ወደ ትግራይ የተጓጓዘ መድሃኒት

ቅርንጫፉ ለ21 ሆስፒታሎችና 26 ጤና ጣብያዎች በቀጥታ ያሰራጨ ሲሆን ለመቀሌ ከተማ ለአራት ሆስፒታሎችና ሁሉም ጤና ጣብያዎች፣ ለዉቅሮ፣ ሀውዜን፣ አድግራት፣ አክሱም ቅድሰት ማርያም፣ ኮረም፣ መሆኒና ለሎች ሆስፒታሎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ በቀጣይም የመደበኛና የጤና ፕሮግራም መድሀኒትና የህክምና ግብዓቶች ለሁመራ፣ አላማጣ እንደሚሰራጭ ተገልጸዋል፡፡

የመቀሌ ቅርንጫፍ ባሁኑ ወቅት ከማዕከላዊ መጋዚን ከተላከው 71 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸዉ መድሀኒትና የህክምና ግብዓቶችን ጨምሮ 350 ሚሊዮን የሚሆን የመደበኛ እና የጤና ፕሮግራም መድሀኒትና የህክምና ግብዓቶች ክምችት ያለው መሆን ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡

Exit mobile version