Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 2.5 ሚሊየን ለሚደርስ ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ ገለጹ

”የትግራይ ህዝብ የባሰ ሰብዓዊ ችግር ውስጥ እንዳይገባ የፌደራል መንግስቱ በከፍተኛ ትኩረትና ቁርጠኝነት አጋርነቱን እያሳየ ነው”


የትግራይ ሕዝብ ካለበት የባሰ ሰብዓዊ ችግር ውስጥ እንዳይገባ የፌደራል መንግሥቱ በከፍተኛ ትኩረትና ቁርጠኝነት አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ መገመቱን ጠቁመዋል።

ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ሙሉ ነጋ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ ጁንታው በስልጣን ላይ በነበረባቸው ወቅቶች በክልሉ ቁጥራቸው ከፍ ያለ የህብረተሰብ ክፍሎች በሴፍቲኔት እየታገዙ ይኖሩ ነበር ። አሁን ደግም በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ ፈላጊ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

የኤሌክትሪክ። የቴሌኮምና ባንክ አገልግሎቶች ተቋርጦ በመቆየቱ ምክንያት ከዚህ ቀደም ድጋፍ የማይፈልጉ ሁሉ አሁን ድጋፍ ፈላጊ ሆነዋል ፤ የፌደራል መንግሥቱ ይህንን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ህብረተሰቡ የተባባሰ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራና እያገዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ሙሉ ገለጻ ከዚህ ቀደም በክልሉ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ጥሩ ቢሆን ኖሮ ለጥቂት ጊዜያት እንኳን ይህንን ችግር ማለፍ ይቻል ነበር፤ ሆኖም ክልሉ ቀድሞም የተጎዳ ስለነበር እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲጨመርበት ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ተከስቷል ብለዋል።

ጁንታው ቡድን ጦርነት የለኮሰበት ወቅት አርሶ አደሩ የዘራውን ምርት በሚሰበስብበት ጊዜ መሆኑ ችግሩን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳባባሰው የተናገሩት ዶክተር ሙሉ፣ በዚህም በክልሉ የተሰበሰበ ምርት የለም ፤ የእርዳታና የድጋፍ ፍላጎቱም ይህንን ሁሉ ከግምት ያስገባ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

“አሁን እንደ መጀመሪያ ገንዘብ ያለውም ሰው እርዳታ ማግኘት ይፈልጋል፤ ሆኖም ባንኮች ወደ ስራ እየገቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ገንዘብ ማውጣት ከጀመረ የተረጂው ቁጥር ይቀንሳል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ግን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ እርዳታ እንደሚፈልግ ይገመታል ፤ እዚህ ላይ ግን ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር ይችላል ” ብለዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version