Site icon ETHIO12.COM

“የእሳት ፖለቲካ” – አዲስ አበባን እየበላ ነው

በሁለት ቀናት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የዕሳት ቃጠሎ በአዲስ አበባ ደርሷል። ቃጠሎውን ማን እያደረሰው እንደሆነ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ውስጥ የተነሣው የእሳት ቃጠሎ አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በህዝብ ጥቆማ ከመያዛቸው ውጪ ስለሌሎቹ ቃተሎዎች የተባለ ነገር የለም።

ቃጠሎዎቹ የደረሱት በአዲስ አበባ ኡራኤል አካባቢ በመኖርያ ቤቶች፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዘሃብ ሆቴል፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማና  በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከል የደርሱት አደጋዎች ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የጣሉ ናቸው።

በተላይዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ሆነ አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የእሳት አደጋ መበራከቱ ” የእሳት ፖለቲካ ተጀመረ?” የሚያሰኝ እንደሆነ አደጋው በዘገቡ ሚድያዎች ዜና ስር አስተያየት እየሰጡ ነው። አንዳንድ ስማቸው በውል ያልተጻፈ ወይም በድብቅ ስም ራሳቸውን የሰየሙ ” እኔ ነኝ ያቃጠልኩት” የሚል አስተያየትና ” ከንቲባ አዳነች ማብራሪያ ትሰታለች” የሚሉ ሽሙጦችም አሉ።

ዘረኝነትና የጎሳ አስተሳሰብ፣ ስልጣን ያጡ አኩራፊዎች፣ ከሽግግሩ ሂደት ጋር ያልተስማሙና በራሱ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባለ የአመለካከት ጥራት ጉድለት እየተናተች ያለችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ እሳት አዲሱ የትግል ስልት ሆኖ ሌላ ምስቅልቅል እንዳይፈጠር እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስተአየት የሰጡም አሉ።አጋጣሚ ሆኖ በተደጋጋሚ እሳት ሊነሳ እንደሚችል በመተቆም መደናገጥ እንደማያስፈልግም የገለጹ አሉ።

ቃጠሎ አንድ

ዛሬ ከቀኑ 7:00 ሰዓት አካባቢ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ውስጥ ተነስቶ የነበረው እሣት በተደረገው ርብርብ እሳቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እና ወደ ሌላ ቦታ ሳይስፋፋ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ።ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የእሣት አደጋው በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው ይህ ስፍራ ለከተማችን ውበት ድምቀት ከሆኑትና እንደ ከተማችንን ከጎርፍ ለመከላከል ከምንጠቀምባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

የተነሣውን እሳት ማጥፋት በርካታ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት እና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች ፣ የመንገዶች ባለስልጣን፣ የአካባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰቡ እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል።እሳት ውስጥ ገብታችሁ እሳት ላጠፋችሁ ሁሉም አካላት በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።ለእስቱ ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት ወ/ሮ አዳነች ቀሪ ስራዎችን በልዩ ትኩረት የምናከውን ሲሆን መረጃዎችን በየወቅቱ ለህብረተሰቡ እናደርሳለን ብለዋል ።ምንጭ የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት

ቃጠሎ ሁለት

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤበትናንትው እለት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከልና ጉለሌ ክፍለ ከተማ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ መነሻ በማጣራት እርምጃ እንደሚወሠድና በቃጠሎው ለተጎዱ ነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ ጠዋት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከል በመገኘት በእሣት ቃጠሎ የደረሰውን ጉዳት ጎብኝተው የተጎዱ ነዋሪዎችን አጽናንተዋል።በሁለቱም አካባቢ የተነሣው እሣት ድንገተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሠባቸው ነዋሪዎች መፅናናት እንዳለባቸው ገልፀው፤ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

“በአደጋው የተቃጠሉ የሱቆች እና የቤቶች ብዛት፣ በጠቅላላው የደረሰው ጉዳት በፖሊስ እየተጣራ ነው” ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ የእሳት አደጋውን መነሻ ለማወቅ በሚደረገው ጥረት እና ለጋራ ሰላም ሲባል መረጃ ያለው ሰው ሁሉ ለህግ አስከባሪ እና ለፖሊስ መረጃውን በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል። ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።

ቃተሎ ሶስት

በአዲስ አበባ ኡራኤል አካባቢ በመኖርያ ቤቶች ላይ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ደረሰ፡፡የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በቦሌ ክፍለ ከተማ ኡራኤል አካባቢ በሚገኙ መኖርያ ቤቶች ላይ ድንገተኛ የእሳት አደጋ መድረሱን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።ባሁኑ ሰአት የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ከፍተኛ እርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡የእሳት አደጋው የደረሰው ከቀኑ 5 ሰአት 30 ደቂቃ ላይ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

በአደጋው መክንያት በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት በተመለከተም መረጃው እንደተጠናቀቀ የምናደርሳችሁ ይሆናል፡፡በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በተከሰቱ አራት አደጋዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ንብረት መውደሙ ይታወሳል።በኡራኤል አካባቢ የደረሰው የአሁኑ አደጋ ባለፉት ሶሰት ቀናት በከተማዋ አምስተኛው የእሳት አደጋ ሆኗል። ሲል የዘገበው ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።

ቃጠሎ አራት

በአዲስ አበባ ቦሌ ዘሃብ ሆቴል አካባቢ ሌላ የእሳት አደጋ ተከሰተ። አደጋው ከደቂቃዎች በፊት ታምሪን መኪና መሸጫ አካባቢ ዘ ሀብ ሆቴል ፊት ለፊት ባለ አንድ መኖሪያ ቤት መድረሱን አይተናል። አደጋውን በቁጥጥር ሰር ለማዋል የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የአካባቢው ሰዎች የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ የእሳት እና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች በቦታው ደርሰው አደጋውን በቁጥጥር ስር ለማዋል በጥረት ላይ ናቸው። ሲል የዘገበው ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።

Exit mobile version