Site icon ETHIO12.COM

“ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ እየተቸገርን ነው” ኦፌኮ

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ

ፓርቲያችን፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከመጀመሪያ ምስረታው ጀምሮ በሰላማዊ ትግል የሚያምን፤ ለወቅቱም ሆነ ለቆዩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች መፍትኼ ለማግኘት ውይይትና ድርድር አስፈላጊ እንደሆኑ አሳውቋል፤ እንዲሁም የመንግስት ሥልጣንን ለመያዝ ከጉልበትና መሳሪያ ኃይል ይልቅ ነፃ፣ ፍትሓዊና በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ተካሂዶ በሕዝብ ይሁንታ ብቻ እንዲሆን ያለንን በጎ ምኞት ስንገልፅ የቆየን ቢሆንም፤ የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከመጥበቡ የተነሳ ፓርቲያችንም ሆነ ሕዝባችን የሚፈለጉት የፖለቲካ አስተዳደር አልመጣም፡፡ የመንግስትና የገዥው ፓርቲ መዋቅር ጥመርታ ከፍተኛና የማያፈናፍን በመሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማቱ ሊጎለብቱና ለተቋቋሙለት ዓላማ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡

ፓርቲያችንም የአገራችን ሕገ መንግስትና ሌሎችም የአገሪቱ ሕጎች በሚፈቅዱት ሁኔታ ተንቀሳቅሰን ፖሊሲያችንና የፖለቲካ ፕሮግራማችንን ለሕዝብ ማስረዳት አልቻልንም፡፡ በእንዴዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለን ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እየቀረበ መጥቷል፡፡ አስቸጋሪ ናቸው የምንላቸውን ነገሮች እንደሚከተለው እንዘረዝራለን፡፡

  1. የምርጫ ቦርዱ መዋቅር ውስጥ ሳይቀር የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተሰግስገውበታል፡፡ ላዕላይ አካሉም ከጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር በዘለለ መስክ ላይ ያለውን ዕውነታ ገምግሞ የመፍትኼ አቅጣጫ ለማመላከት ፍቃደኛነቱ አንድም አናሳ ነው ወይም ጨርሶ ባለመኖሩ በቦርዱ ላይ ያለን እምነት እየተሸረሸረ ሄዷል፡፡
  2. መጪውን ምርጫን አስመልክቶም፤ ምንም እንኳን የዜጎችን የሥራ ዕድል ማግኘት የምንደግፍ ቢሆንም ምርጫን የመሰለ ሀገራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙ ሰዎች የሚወዳደሩበትን ከፍተኛ ሥራ ላይ ልምድ የሚጎድላቸው ዜጎች እየተመደቡ ስለሆነ ስለተአማኒነቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ ገብቶናል፡፡
  3. አሳሪ የሆኑ የአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ ቁጥሮች 2(29) እና 33(ለ) ምንም ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ወደ ምርጫ መግባቱ የምርጫውን ከአድልአዊነት በፀዳ መልኩ ሊከናወን ስለመቻሉ እንድንጠራጠር አስገድዶናል፡፡
  4. በአብዛኛው የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ጽ/ቤቶቻችን ተሰብረውና ተዘርፈው ሌሎችም ተዘግተው የት ቦታ ተኩኖ አባላት፣ ዕጩዎችና ታዛቢዎችን ማሰባሰብ እንደሚቻል መገመት አሰቸጋሪ ሆኖብናል፡፡
  5. ከሥራ አስፈፃሚ ጀምሮ በተለያዩ የመዋቅር እርከኖች ላይ የሚገኙና ሥራዎችን ሊያስተባብሩ፣ ተወዳዳሪዎችንና ታዛቢዎችን የሚመርጡ የኦፌኮ አባላት ታስረው ወይም ከሚፈጸምባቸው ማስፈራሪያ የተነሳ አከባቢያቸውን ጥለው በሄዱበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን፤ በተለይም ደግሞ የታሰሩ አባሎቻችን በነሱም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ከሚደርስ ጫና የተነሳ ጤንነታቸውና ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ባለበት ሁኔታ ኦፌኮ ምርጫ መወዳደር ይችላል ብሎ የሚፈርድብን ማንም ሰው ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡
  6. በአገሪቱ ውስጥ ሰላም በመታጣቱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በኮማንድ ፖሰት በታጠረበትና በነፃነት ተንቀሳቅሰን ፖሊሲያችንና የፖለቲካ ፕሮግራማችንን ለሕዝብ ባላስተዋወቅንበት ሁኔታ ውስጥ መጪውን ስድስተኛውን አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ እየተቸገርን መሆኑ ታውቆ፤ ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን መፍትኼ ከወዲሁ እንድፈልግልን ደጋግመን እንጠይቃለን፡፡

ከአክብሮት ሠላምታ ጋር!

መረራ ጉዲና (ፕ/ር)
የኦፌኮ ሊቀ መንበር
አዲስ አበባ

Exit mobile version