Site icon ETHIO12.COM

ችግር ሲገጥም ልዩነትን ወደጎን በማድረግ አንድ መሆን ግድ ነው

‘’የየትኛውም አገር ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሙን የሚነኩ ጉዳዮች ሲገጥሙት ያለውን ልዩነት ትቶ አንድ ከመሆን ወደኋላ ማለት የለበትም’’ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ

(ኦነግ) ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ

የገዘፉ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ኢትዮጵያ ለውጭ ጠላት ተጋላጭ የምትሆንበትን ዕድል እየፈጠረ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።ህዝቡ አንድነቱን አስጠብቆ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በሁሉም አቅጣጫ የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ጠይቀዋል።በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ያለመረጋጋት እያጋጠመ ይገኛል።ይህ ሁኔታ በተለይም የአገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማይፈልጉ የአገር ወስጥና የውጭ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ትኩረቱን ባደረገበት ጊዜ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ገፍታ መግባቷ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት አካባቢ በረጅም ጊዜ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የሁለቱ አገሮች ዜጎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች መነሳታቸው አዲስ ክስተት እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የሁለቱ አገሮች መንግስታት ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት የጋራ የድንበር ኮሚሽን ከማቋቋም ጀምሮ ተደጋጋሚ ውይይቶችን እያደረጉ ባለበት ሁኔታ ነው ሱዳን ወታደሮቿን በኢትዮጵጵያ ድንበር ላይ ያሰፈረችው።በተለይ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ባላቸው ልዩነት የኢትዮጵያን ሰላም የሚያደፈርሱ ነገሮችን ሁሉ ከመደገፍ ወደኋላ እንደማይሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያነሳሉ።

በአገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችና የገዘፉ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ደግሞ ለፍላጎታቸው መሳካት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ነው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የገለጹት።የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ ‘’የየትኛውም አገር ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሙን የሚነኩ ጉዳዮች ሲገጥሙት ያለውን ልዩነት ትቶ አንድ ከመሆን ወደኋላ ማለት የለበትም’’ ይላሉ።

በተለይ የአገር ዳር ድንበር ሲደፈር ጉዳዩን በግዴለሽነት ማየት አገር ከማፍረስ አይተናነስም ነው ያሉት።በአገር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩም በጋራ ጉዳዮች ላይ አንድነትን መሸርሸር አገሪቱን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት ሰፊ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ‘’አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ርብርብ ልናደርግ ይገባል’’ብለዋል።“የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና የማይፈልጉ ኃይሎች በአገሪቷ የሚከሰቱ ችግሮች እንዲባባሱ ድጋፍ ማድረጋቸው የተለመደ ነው” ያሉት አቶ በቴ ይህም በአካባቢው የበላይ ሆኖ ለመውጣት የሚደረግ ትግል መሆኑን አንስተዋል።

Exit mobile version