Site icon ETHIO12.COM

አህያ አህይትን “አስገድዶ ደፈረ” ባለቤት ተቀጣ

እዚሁ እኛ አገር…አህያው አህይት ላይ በወጣ፣ ባለቤቱ በፍ/ቤት 425 ብር ተቀጣ… የፍ/ቤቱን ውሳኔ የዘገበው ጋዜጠኛ፣ የክልሉን ስም አጥፍተሃል ተብሎ ታሰረ.(ልቦለድ የሚመስለው የጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ እውነተኛ ገጠመኝ)..በጋዜጠኝነት ህይወቴ ካጋጠሙኝ ሁሉ፣ ሁልጊዜም የማይረሳኝ አንድ አስገራሚ የፍርድ ውሣኔ ነበር፡፡

ጉዳዩ የተፈጸመውና የፍርድ ውሳኔው የተላለፈው በአንድ የአገራችን ክልል ዋና ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ የፍርድ ውሳኔው እንኳንስ በሕግ ባለሙያ ይቅርና፣ በማንም ስለ ህግ ዕውቀት የሌለው ሰው እንኳ ሊሰጥ የማይችል እጅግ አስገራሚ ውሳኔ ነበር – በእንስሳ ላይ የተሰጠ ውሣኔ ነው፡፡“አንድ ወንድ አህያ አንዲት ሴት አህያን አስገድዶ ደፍሯልና ባለቤቱ ሊጠየቅ ይገባል” የሚል ክስ ነበር የቀረበው፡፡

ከሳሽ የሴቷ አህያ ባለቤት ነበር::“ወንዱ አህያ አህያዬን አስገድዶ በመድፈር ላደረሰባት ጉዳት የወንዱ አህያ ባለቤት ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል” በማለት ነበር የሴቷ አህያ ባለቤት ክስ የመሰረተው፡፡የወንዱ አህያ ባለቤት በክሱ በጣም ግራ ተጋባ…“ምንድነው የምታወሩት? ይህ እንዴት ካሳ ሊቀርብበት የሚገባ ጉዳይ ሆነ?…” ብሎ በጣም ተከራከረ፡፡ሆኖም ፖሊሶች ተከሳሹንም ደፈረ የተባለውን አህያም ወስደው አሰሩዋቸውና፣ ፍርድ ቤት አቀረቧቸው – ክርክሩ ቀጠለ፡፡

በስተመጨረሻም…የወንዱ አህያ ባለቤት በሁኔታው በጣም በመበሳጨቱ፤ “የደረሰውን ጉዳት መጠን የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ ይምጣልኝና ካሳውን እከፍላለሁ” አለ፡፡ክስ አቅራቢው የሴቷ አህያ ባለቤት መልስ አላጣም…“እዚህ አገር ያሉ የእንሰሳት ሃኪሞች ይህንን ዓይነት የሕክምና ማስረጃ ለመስጠት አቅሙ ስለሌላቸው አህያዋ ተጭና ወደ ደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ተቋም ሄዳ እንድትመረመርና ማስረጃው እንዲሰጠኝ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡

ሁኔታው የወንዱን አህያ ባለቤት በእጅጉ አበሳጨው:: ሆኖም ምንም ማድረግ አይችልም ነበርና፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ እንደሚቀበል ያስታውቃል።ከዚህ ሁሉ በኋላ…የፍርድ ቤቱ ዳኛ ገራሚ ውሳኔ አስተላለፈ…“የወንዱ አህያ ባለቤት፣ ተገዳ ተደፈረች ለተባለችው ሴት አህያ ባለቤት 425 ብር ከ25 ሳንቲም የጉዳት ካሳ እንዲከፍል” ሲል ውሳኔ ሰጠ፡፡(አህያዋ በወቅቱ 100 ብር እንኳን አታወጣም ነበር )፡፡የወንዱ አህያ ባለቤት ግን፣ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ይጠይቃል::

በዚህ መካከል ነበር፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተ መረጃ የደረሰኝ…ጉዳዩን መከታተል ጀመርኩ… ከወንዱ አህያ ባለቤት፣ ከፖሊስ ጣቢያው፣ ከአካባቢው ሰዎችና ስለ ጉዳዩ ከሚያውቁ ሰዎች ሁሉ መረጃዎችን አሰባስቤ፣ ውሳኔውን ወደሰጠው ዳኛ አመራሁ፡፡

“በአገራችን የፍትሐ ብሔርም ሆነ የወንጀል ሕግ ላይ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ክስ ሊቀርብም ሆነ ተከሳሹን ሊያስቀጣ የሚችል ጉዳይ የለም፤ ታዲያ አንተ በምን መነሻ እና እንዴት ነው ይህንን ውሳኔ ልትሰጥ የቻልከው?” ስል ጠየኩት፡፡“አንተ ለመሆኑ ማነህ?…” አለኝ፡፡ጋዜጠኛ መሆኔን ነግሬው፣ መታወቂያዬን አሳየሁት፡፡“ውሰዱና እሰሩት!…” ሲል አዘዘ፡፡አሰሩኝ፡፡

ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ የክልል ከተማ ላይ ነው፡፡ ተቀጥሬ እሰራበት ለነበረው “እፎይታ” መጽሔት እንደታሰርኩ የሚገልጽ መልዕክት ወደ አዲስ አበባ ላክሁ፡፡ በወቅቱ አለቃዬ የነበረው ተስፋዬ ገብረአብ ወደ ክልሉ ስልክ ደውሎ አነገራቸውና ከእስር ተፈታሁ፡፡

እንደተፈታሁ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ መጣበት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሄድኩና ጠየኩ፤ ጉዳዩ ገና እንዳልደረሳቸው ነገሩኝ፡፡ይህን ተከትሎም የአህያዋን ጉዳይ በተመለከተ “እፎይታ” መጽሔት ላይ ዘገባ ሰራሁ፡፡ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ደግሞ በመጽሔት ላይ ያወጣሁትን ዘገባ ወስዶ ዘገበው፤ ጉዳዩ ብዙዎችን በስፋት ማነጋገር ጀመረ፡፡ይሄኔ ነው፣ ጉዳዩ የተፈጸመበት ክልል ፕሬዚዳንት በሰጡት ትዕዛዝ በፖሊስ ተያዝኩና በድጋሜ ታሰርኩ፤ የክልሉን ስም አጥፍተሃል ተብዬ ማለት ነው፡፡

ጥቂት ቆይቶ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ስልክ እየተደወለ ጫና ሲደረግባቸው ፍርሃት አደረባቸውና ከእስር እንድፈታ አደረጉኝ፡፡ ይህም ፍትህ ምን ያህል የተዛባ እንደነበር የሚያመላክት ጉዳይ ነው፡፡.(የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ለንባብ ካበቃችውና ጋዜጠኛ Metasebiya Kassaye ከለንደኑ “ሉሲ ሬዲዮ” መስራችና ባለቤት ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ ጋር ካደረገችው ቃለመጠይቅ የተቀነጨበ ነው)

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

Exit mobile version