Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያና ሱዳን አለመግባቶቻቸውን በጋራ ውይይትና ስምምነት ሊፈቱ እንደሚገባ ሱዳናዊው የታሪክ ምሁር ተናገሩ

ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀውን የጋራ ግንኙነታቸውን መሰረት በማድረግ የድንበር አለመግባቶቻቸውን በውይይትና ስምምነት ሊፈቱ እንደሚገባ አንድ የሱዳን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ተናገሩ።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮ-ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ኮንፍረስ ዛሬ አካሂዷል፡፡ በኮንፍረንሱ የተገኙት የሱዳን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና አርት ምሁር ዶክተር ኦማር አልአሚን “ኢትዮጵያና ሱዳን ረዥም ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያላቸው ታላቅ ህዝቦች ናቸው” ብለዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በተለይ ከአባይ ወንዝ ጋር ታሪካዊ ቁርኝት እንዳላቸው አውስተው ይህ ዘመናትን የዘለቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በጥቃቅን የድንበር ላይ ችግሮች ሊደናቀፍ እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡

የሀገራቱ መንግስታትና ፖለቲከኞች የድንበር ጉዳይን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ በውይይትና ድርድር በመፍታት የህዝቦቻቸውን ሠላማዊ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ጦርነትና ግጭቶችን የችግሮች አማራጭ የመፍቻ መንገዶች ማድረግ ተገቢነት የለውም” ያሉት ምሁሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የማይለያዩና አንድ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ግንኙነት በማጠናከር በኩል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ የሱዳን ዩኒቨርሲቲ ከጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ያመለከቱት ምሁሩ፤ ሱዳን በቅኝ ግዛት ስምምነቱ ወቅት በአባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚ አልነበረችም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ሱዳንን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ከማድረግ በዘለለ ሰፊ የእርሻ መሬቷን በመስኖ አልምታ እንድትጠቀም የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአባይ ወንዝ ከፍተኛ የውሃ ምንጭና የሁለቱን የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚያስተሳስር በመሆኑ ሀገራቱ በትብብር መንፈስ በጋራ ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ሂውማኒቲ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አገኘሁ ተስፉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በጎ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችን በጋራ ለማስተሳሰር እንዲቻልም በጎንደርና ሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች የአማርኛና አረብኛ ቋንቋዎች በሥርዓተ ትምህርት ተደግፈው እንዲሰጡ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

የኮንፍረንሱ ዓላማ ሁለቱ ሀገራት በታሪክ ፣ባህልና ንግድ ያላቸውን ለዘመናት የዘለቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ረገድ የሀገራቱ ምሁራን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኮንፍረንሱ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ታሪካዊ ግንኙነት የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎችም በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የሱዳን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁራን ፣ የጎንደር ዩኒቨርሰቲ የታሪክና የባህል ምሁራን እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች በኮንፍረንሱ መሳተፋቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከጎንደር ዘግቧል።. የካቲት 09/2013(ኢዜአ)

Exit mobile version