Site icon ETHIO12.COM

የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ሙከራ ምርት ሊሸጋገር ነው፡- ስኳር ኮርፖሬሽን


በግንባታ ሂደት ላይ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ከሶስት ወራት በኋላ ወደ ሙከራ ምርት እምንደሚሸጋገር ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ግንባታው ለአንድ ዓመት መጓተቱ የተገለጸው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ፣ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ቀሪ የግንባታ ሂደቶችን አልፎ የፊታችን ግንቦት ወደ ሙከራ ምርት እንደሚገባ ኮርፖሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም በተለይ ለኢቢሲ እንደገለፁት፣ በኮርፖሬሽኑ የተካሄደውን የለውጥ ሥራ ተከትሎ የተጀመሩትን የስኳር ፋብሪካዎች ለመጨረስ ነባሮችን ደግሞ የማምረት አቅም ለማሳደግ ግብ ተጥሎ ሲሠራ ነበር ብለዋል፡፡

የስኳር አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ሀገራዊ የስኳር ምርት በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 2.5 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 3.2 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ከሰም፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ኦሞ ቁጥር ሁለት እና ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ በመግባታቸው የስኳር አቅርቦት እጥረትን መቀነስ እንደተቻለም ነው አቶ ጋሻው የገለፁት፡፡

በግንባታ ላይ ያለው ኦሞ ቁጥር አንድ የስኳር ፕሮጀክት የግንባታ አፈጻጸሙ 83 በመቶ፣ አሞ ቁጥር 5 ደግሞ ግንባታው 27 በመቶ መድረሱም ተመልክቷል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት ግንባታው የዘገየው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 93 በመቶ፣ ምዕራፍ ሁለት ግንባታ ደግሞ 85 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

ኮርፖሬሽኑ የስኳር ምርትን ለማሳደግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የነባር የስኳር አምራች ማሽኖችን ብልሽት በመጠገን፣ በቂ የሸንኮር አገዳ አቅርቦት እንዲሁም የመፍጨት እና ስኳር የማምረት አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉን የስኳር ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ EBC

Exit mobile version