Site icon ETHIO12.COM

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጥብቅ መመሪያ አወጣ – ጥይት መተኮስ ተከለከለ፤ በህግ ያስቀጣል

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን ያስከብራል!በኢትዮጵያ የቱሪስት ማዕከላት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ከተሞች አንዷ በሆነችው ጎንደር ከተማ አልፎ አልፎ ሰበብ እየተፈለገ የጥይት ተኩስ ይሰማል። በሕግ ማስከበሩ ሂደት የተገኙ ድሎችን ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን በተኩስ እሩምታ የሚገልጹ አካላት በሰላማዊቷና የቱሪስት መዳረሻ ለሆነችው ከተማችን የማይመጥን የነዋሪውን ህዝብ ተረጋቶ በሰላም መኖር የሚረብሽ፤ ቱሪስትን የሚያስበረግግ ተግባር ሁኖ ይስተዋላል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ከተገኘው ድል ጋር በተያያዘ ያለውን የአሸናፊነት ስሜት በመረዳትና ይቆማል በሚል በማስጠንቀቂያ ማለፉ አይዘነጋም።ሆኖም ግን፤ ይህ ድርጊት ሕገወጥ፣ የከተማችን ገፅታ የሚጎዳ፣ ጎንደርን በመውደድ የመጡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችንና ፍጹም ሰላማዊ ሕዝቦችን የሚረብሽ በመሆኑ የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የፀጥታ ኃይላችን ከአሁን በኋላ ሳያወላውል የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር፣ ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ማሳወቅ ይወዳል።

በዚህ የሰለጠነ ዘመን፣ ያውም የሥነ-መንግሥትን ውቅርና ይዘት በምታውቀው በጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ደስታን በተኩስ እሩምታ መግለፅ የማይጠበቅና አሳፋሪ ድርጊት ነው። ይህ ታሪካችንን የማይመጥን አፍለኛ ባህሪ ነው።በከተማችን የሚገኙ ክልላዊ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተረጋግተው ስራቸውን በሚያከናውኑበት፤ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን በሚከውኑበት፤ ለከተማችን ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የምርምር ማእከላት ተረጋግተው ስራቸውን በሚሰሩበት በዚህ አስፈላጊ ወቅት ላይ እንዲሁም የንግድ ማኅበረሰባችንና መላው ህዝባችን ስራውን ለማከናወን ላይ ታች ብሎ በሚሰራበት በዚህ ጊዜ ከተማችንን መረበሽ ህዝባችንን እንደመናቅና እንደማዋረድ የሚቆጠር በመሆኑ የሚፈጥረው ጉዳትና መረበሽ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ይህን ሕገወጥ ድርጊት ሽፋን በማድረግም ወንጀል ለመስራት የሚጥሩ አካላት እንደሚኖሩ የከተማ አስተዳደራችን ይገነዘባል።

በመሆኑም ደስታን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ ሲቻል፣ በጥይት ተኩስ እንገልፃለን የሚሉ አካላትን ለሕግ በማቅረብ የከተማችንን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት እናረጋግጣለን።ሕዝባችንም ይህንን አውቆ፣ በሕገወጥ ተግባራቸው ከተማችንን እየጎዱ ያሉ አካላትን ስርዓት ለማስያዝ መንግሥት በሚያደርገው ህግን የማስከበር ዘመቻ ከጎናችን እንዲሆን ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።በተለይ የእምነት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ በአጠቃላይ ሕዝባችን ከነገ ጀምሮ ይህን ሕገወጥ ድርጊት ዳግመኛ እንዳይፈፀም ሕግ ለማስከበር በምናደርገው እንቅስቃሴ ከጎናችን እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።ስለሆነም የከተማችን የጸጥታ ኃይል የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እያስጠበቀ መሆኑ ታውቆ ሕዝባችንም ሆነ ጎብኝዎች ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባቸው አደራ እንላለን።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር

Exit mobile version