Site icon ETHIO12.COM

በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የሱዳንና የግብፅ እጅ እንዳለበት ተገለጸ


በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶችን በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በግጭቱ ውስጥ የሱዳን እና የግብጽ ድጋፍ እንደነበረበት የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አብዱላሂ ሀሙ ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው ይህንን የገለጹት ኮሚቴው ከትግራይ ክልል ውጭ በመተከል እና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን ተመልክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

በሱዳን ድንበር ታጣቂዎችን የማሰልጠን እንቅስቃሴ እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ ሲከናወን እንደነበር ከሕብረተሰቡ እና ከመተከል ኮማንድ ፖስት መረዳታቸውን ነው አቶ አብዱላሂ በመግለጫቸው ያብራሩት፡፡

የተፈጠረው ግጭት የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ረዘም ያለ ዝግጅት የተደረገበት እና በኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ ሌላ አጀንዳ የነበራቸው አካላት “ክልሉ ሊፈርስ ነው፤ ልትወረሩ ነው፤ ታጠቁ፤ ተዘጋጁ፤” እያሉ ይቀሰቅሱ እንደነበር ሰብሳቢው አክለው ጠቅሰዋል፡፡

በአብዛኛው ወረዳዎች የሸሹ ታጣቂዎች የተመለሱ መሆኑን እና 3 ሺ የሚሆኑ ታጣቂዎች ደግሞ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ እጃቸውን መስጠታቸውን እና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የተደረጉ መሆኑንም አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡

በመተከል እና አካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ68 ሺህ በላይ የሚሆን የጉሙዝ ማኅበረሰብ ሸሸቶበት ከነበረው ጫካ እንደተመለሰም ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሚሊሻዎችን በመመልመልና በማሰልጠን የዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ አብዱላሂ ጠቅሰዋል፡፡

የጥፋቱ አካል የነበሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን ከቦታቸው በማንሳት ለሕግ የማቅረብ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ከኮማንድ ፖስቱ መረዳታቸውን አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ከተለያዩ የአካባቢው የሕብረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ እንዳልሆነና ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት የፈጠሩት ግጭት መሆኑን መረዳታቸውን አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በተጠለሉባቸው የተለያዩ ቦታዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ነው ሰብሳቢው የተናገሩት፡፡

ሰብዓዊ ድጋፉ ባልተቆራረጠ መልኩ እንዲከናወን ከፌደራል እና ከክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ-አመራር ኮሚሽ ጋር በጋራ የሚሰራ የቴክኒክ ኮሚቴ ቡድን በማዋቀር እየተሰራ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍ ከማለቱ የተነሳ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ የማይደርስበት ሁኔታ መኖሩንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 125 ሺህ እንደሆነ ነው አቶ አብዱላሂ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡

በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ለተፈናቃዮች እንዲደርስ መንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አቶ አብዱላሂ ጥሪ አቅርበው፣ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቦታቸው የመመለስ፣ የስነ-ልቦና ግንባታ ስራዎችን የመስራት እና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ስራ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማሳሰባቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Exit mobile version