Site icon ETHIO12.COM

“አንድነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ ነገና ከነገ በስቲያ በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው

”አንድነት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ ነገና ከነገ በስቲያ በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ መሆኑን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ።“በውጭ ሃገራት የሚነዙ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች የኢትዮጵያን ገጽታ ከማጠልሸት ባለፈ የአገር ሉዓላዊነትን የሚዳፈሩ በመሆናቸው እውነታውን ለማሳወቅ እንታገላለን” ሲሉ ነው ኢትዮጵያውያኑ የገለጹት፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አቶ ጣሰው መልዓከህይወት ከዋሽንግተን ዲሲ እንዲሁም አቶ ብንያም ጌታቸው ከካሊፎርኒያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አስተባባሪዎቹ መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የጁንታው ርዝራዦችና የእነርሱ ደጋፊ ሚዲያዎች አለምአቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።“መንግስት፣ ዳያስፖራውና የተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ትግራይን መልሶ በማቋቋምና በሰብዓዊ ድጋፎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንና እውነታዎችን ትተው የሀሰት መረጃ እያሰራጩ ነው” ብለዋል።

ድርጊቱ የኢትዮጵያን ገጽታ ከማበላሸት ባለፈ በአገር-ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደመሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል።በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታም ሆነ በህዳሴ ግድብ ላይ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ለማድረስ የሚሞክሩትን ተጽዕኖ እንደማይታገሱ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።ለዚህ ደግሞ ነገና ከነገ በስቲያ በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች ኢትዮጵያን በተመለከተ በአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል።

በሰልፉ ላይ የተለያዩ መልዕክቶች የሚተላለፉ ሲሆን ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።በሰልፎቹ የሚተላለፉት መልዕክቶች በዋናነት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ መግባት እንደማያስፈልግ የሚያስገነዝቡ እንደሚሆኑም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version