Site icon ETHIO12.COM

” የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለፁ:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይትም የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር በአስመራ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው::ሁለቱ መሪዎች በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተወያይተዋል::

በጥቅምት 25፣ 2013 በሕወሐት ውስጥ የተሰባሰበው የወንጀል ቡድን፣ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የከሸፈ ክህደት ፈጽሟል። በዚህም ሀገርን ወደ ሁከት በመምራት ሥልጣንን ለመያዝ መሞከሩ ይታወሳል። የሀገሪቱ ትልልቅ የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች በሚገኙበት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እና የመከላከያ ሠራዊታችንን አባላት ያለ ርኅራኄ መግደሉ እና ማፈኑ የፌዴራል መንግሥት ሳይፈልግ ወታደራዊ ርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል። በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሕወሐት ወንጀለኛ ቡድን በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ላይ ሮኬቶችን መተኮሱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይም በኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ ሮኬቶችን ተኩሷል። ይህም የኤርትራን መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ በመግባት ከተጨማሪ ጥቃቶች ራሱን እንዲከላከል እና ብሔራዊ ደኅንነቱን እንዲጠብቅ አነሣሥቶታል፡፡መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ አሥመራ ተጉዤ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረግነው ውይይት፣ የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ወዲያውኑ ተክቶ የድንበር አካባቢዎችን ይጠብቃል፡፡ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና በኢኮኖሚ ትብብር ፍላጎታቸው ላይ አብረው መሥራታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ በ2010 ዓ.ም. በተጀመረው መሠረት በሁለቱ ሀገራት መካከል በመተማመን መንፈስ መልካም የጉርብትና ግንኙነታችንን መገንባታችንን እንቀጥላለን፡፡ በተለይም፣ በትግራይ ክልል እና ከድንበር ማዶ ባሉ ኤርትራውያን ወገኖቻችን መካከል በመተማመን ላየ የተመሠረተ ግንኙነትን መመለስ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የህወሃት የወንጀል ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሀገር በማተራመስ ሥልጣን ለመያዝ የከሸፈ ሙከራ ማድረጉን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል::

ቡድኑ ሰሜን እዝን በማጥቃት የመከላከያ አባላትን በጭካኔ በመግደል እና በማፈን በፈፀመው እኩይ ተግባር የፌዴራሉን መንግሥት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው እንዲገባ አስገድዷል ፡፡የእዙን ጥቃት ተከትሎ የህወሃት ቡድን በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ሮኬቶችን ተኩሷል፡፡

በተመሳሳይም ይህ የህወሃት የወንጀል ቡድን ወደ የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሮኮት ተኩሷል::ይህ ጥቃትም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ድንበር አቋርጦ እንዳይገባ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ብሄራዊ ደህንነቱን ለማስጠበቅ እንዲንቀሳቀስ አድርጏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ላይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይትም የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማምቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል የድንበር አካባቢዎችን ለመጠበቅ ስፍራውን ወዲያው ይረከባል ነው ያሉት:: ጠቅልይ ሚኒስትር አቢይ በሁለቱ አጋር ሀገራት መካከል መተማመን እና መልካም የሆነ የጉርብትና መንፈስ መገንባታችንን እንቀጥላለን ብለዋል::

በተለይም ይህን በመተማመን ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ድንበር አካባቢ በሚኖሩ በትግራይ ክልል እና ኤርትራውያን ወገኖቻችን መካከል መመለስ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

(ኢዜአ)

Exit mobile version