Site icon ETHIO12.COM

ከምርጫ በሁዋላ የመንግስት ተቋማት አወቃቀር ይቀየራል፤ የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ይወስዳሉ

. የመንግስት ሠራተኞች ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ይወስዳሉ

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከምርጫው በኋላ የመንግስት ተቋማትን አወቃቀር ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ። ከመጪው ሚያዝያ 2013 ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንደሚሰጥ ተጠቆመ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስን ጠቅሶ ኢፕድ እንዳለው ከምርጫው በሁዋላ የመንግስት ተቋማት አወቃቀር ብቻ ሳይሆን በቀጣዮቹ ዓመታት የመንግስት ተቋማት የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች በጥልቀት ይፈተሻሉ።ተመሳሳይ ስራና ዓላማ ይዘው የሚሰሩ ተቋማት ወደ አንድ የሚመጡበት ሁኔታም ይኖራል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚዘጋጀው ምዘናው ብቁና ተወዳዳሪ ሠራተኛ ለማፍራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ መንግስት ተቋማት የሚገቡ ሠራተኞችን ሙያዊ ብቃት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ምዘናው ለሁሉም የመንግስት ተቋማት እንዲያገለግል የጋራ መስፈርት ወጥቶለት መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።ወደ መንግስት ተቋማት አዲስ ለሚገቡትም ሆነ ለነባር ሠራተኞች የብቃት ምዘናውን ለመስጠት በቂ ዝግጅት እስከሚደረግ ከታሰበው በላይ ጊዜ መውሰዱንም ኮሚሽነር በዛብህ ገልጸዋል።ይሁንና ስለምዘናው የነበሩ ብዥታዎችን የማጥራትና ምዘናው የሚካሄድበት ቦታና ሁኔታም በመመቻቸቱ ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ ይካሄዳል ነው ያሉት።

በአንዳንድ ተቋማት ሲሰጥ የቆየው የብቃት ምዘና በአዲሱ የምዘና መስፈርት የሚካተት እንደሚሆንና ምዘናውን በግል መስጠት የሚፈልጉ ተቋማትም ከኮሚሽኑ ጋር መዋዋል እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ሲቪል ሰርቪሱን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ይታወል።

Exit mobile version