Site icon ETHIO12.COM

ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆምና መንግስት ህግ እንዲያስከብር ፓርቲዎች አሳሰቡ


ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ጥቃት እንዲቆምና መንግስት ህግ እንዲያስከብር አምስት ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ አሳሰቡ፡፡

ፓርቲዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት በማውገዝ መንግስት ህግ እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቀቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ እናት ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የፌዴራሉ መንግስትና የየክልሎች መንግስታት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በእንዲህ አይነት አገራዊ አደጋ ወቅት በጋራ እንደሚሰሩም በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በጥቃቶች ላይ በሚሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አመራሮች ሆነው በጥቃቱ የተሳተፉትና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡን መንግስት በፍጥነት አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡

በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለማውገዝና ለማጋለጥ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልሎች ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦች መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ጥቃቱን የማስቆምም ሆነ ለተጎጂዎች አስቸኳይ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት የመንግስት ቢሆንም ለህዝቦች ድምጽ በመሆን መንግስት ላይ ግፊት እንደሚያደርጉ ፓርቲዎች በጋራ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡

በዋለልኝ አየለ – (ኢ.ፕ.ድ)


Exit mobile version