ETHIO12.COM

ቱርክ ስትደርስ 1.6 ኪ.ግ ኮኬን የተገኘባት የበረራ አስተናጋጅ ታስራለች፤ አደራውን ስትቀበል ኮኬን ስለመኖሩ “አላውቅም” ብላለች

ሰላማዊት እጅጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ ናት። እህቷን ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳለው በአደራ እንድታደርስ የተሰጧት ስዕሎች ውስጥ ኢስታንቡል ስትደርስ ኮኬን ተገኝቶባት ታስራለች። ቤተልሄም “አደራ አድርሺልኝ” ባይዋን አታውቃትም። በምን ዓይነት ውል አድርሺልኝ እንዳለቻት አልገለጸለችም። ግን ትንሽ ብር ተከፍሎ ” አድርሱልኝ” ማለት የተለመደ መሆኑንን ተናግራላች።

ቢቢሲ – የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሆነችው ሰላማዊት እጅጉ “በአደራ ወደ ቱርክ የወሰደቻቸው ሁለት ስዕሎች ላይ ኮኬይን ተገኝቶባቸዋል” በሚል በእስር ላይ እንደምትገኝ ቢቢሲ ከቤተሰቦቿ መረዳት ችሏል።

ታናሽ እህቷ ቤተልሄም እጅጉ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ሰላማዊት በአሁኑ ወቅት በቱርኳ ከተማ ኢስታንቡል 1.6 ኪሎግራም የሚመዘዝን ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዛ ስትገባ ተገኝታለች በሚል ከታሰረች 13 ቀናትን አስቆጥራለች።

በኢስታንቡል አየር ማረፊያ ስትደርስ በቁጥጥር ስር የዋለችው ሰላማዊት እጅጉን ወደ አገሯ ለመመለስ በአየር ማረፊያው ከሚገኙ የፀጥታ ኃይሎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ለመደራደር በቱርክ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካ እንዳልቻለ አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ የኢስታንቡል ቆንስላ ጄኔራል ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ስለ ክስተቱ ከቤተሰቦቿ የተሰማው….

እለቱ ረቡዕ መጋቢት 15፣ 2013 ዓ.ም ነበር። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሆነችው ሰላማዊት እጅጉ ወደ አመሻሹ አራት ሰዓት ላይ ነው ወደ ቱርክ የበረረችው።

ከዚያ ቀደም ብሎ ግን አንዲት ሴት ሁለት በቆዳ የተሰሩ ባህላዊ ስዕሎችን በአደራ እንድታደርስላት በስልክ ጠየቀቻት። ቤተልሔም እንደምትናገረው እህቷ በወቅቱ “አልወስድም” በማለት አንገራግራ የነበረ ቢሆንም ሁልጊዜም የምትልካቸው ስዕሎች እንደሆኑ ግለሰቧ ነግራ አግባባቻት።

በዕለቱም ስዕሎቹን ውሰጂልኝ ያለቻት ግለሰብ “ጠብቂን አሁን እንልካለን” እያለች እንዳስረፈደቻትና የአየር መንገድ ሰርቪስ መኪናም እንዳመለጣት ታወሳለች።

በመጨረሻም ግለሰቧ እንደምታደርሳትና መኪናም እንደምትልክ ነገረቻት። መኪናውን ይዞ የመጣው የደወለችላት ግለሰብ ሳትሆን፣ ሌላ አሽከርካሪ ነበር።

ሁለት በቆዳ የተወጠሩና፣ ዳር ዳራቸው ፀጉር ያላቸው ባህላዊ ስዕሎችን ግለሰቡ ሰጣት። አርፍዳም ስለነበር እቃውን ለማየትም ሆነ ለመፈተሽ ጊዜው እንዳልነበራት የምትናገረው ቤተልሔም፣ ሻንጣዋ ላይ አስገብታ ወደ በረራዋ አቀናች ትላለች።

አዲስ አበባ አየር ማረፊያ ምንም ያላጋጠማት ሰላማዊት፣ ኢስታንቡል ስትደርስ በቁጥጥር ስር ዋለች። ስለ ጉዳዩ ምንም እንደማታውቅና “ስዕሎቹን በአደራ አድርሺልኝ” እንደተባለች ተናግራ ይቀበሏታል የተባሉ ሰዎችን ብታስይዝም ግለሰቦቹ ሊያምኑ እንዳልቻሉም ቤተልሄም ታስረዳለች።

ኢስታንቡል በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ፖሊሶች፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዷት ለምና ለባለቤቷ መደወሏንና “ያመጣሁት እቃ ውስጡ አደንዛዥ ዕፅ ነው ብለውኛል” በማለት እያለቀሰች መናገሯን ቢቢሲ ከእህቷ ሰምቷል።

በወቅቱ ምን አይነት አደንዛዥ ዕፅ እንደነበር እንደማታውቅና ምርመራ ከተደረገም በኋላ ነው ኮኬይን መሆኑን አሳወቋት። ለሁለተኛ ጊዜም ፖሊስ ለቃለ መጠይቅ ይዘዋት በወጡበት ወቅት ፖሊሶቹን ለምና ለባለቤቷ ደውላለታለች። እስካሁን ድረስ ቤተሰቦቿ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ማናገር የቻሉት።

ስእሎቹን “በአደራ አድርሺልን” ብላ የደወለችላት ግለሰብ ጋር እውቅና አላቸው ወይ ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላት ጥያቄ ቤተልሔም ስትመልስ፣ እንደማታውቃትና በስልክ አንዲት ሴት እንደደወለችላት ትናገራለች።

ከዚህ ቀደምም ቢሆን የበረራ አስተናጋጆች ወደተለያዩ ውጭ አገራት በሚጓዙበት ወቅት የአደራ እቃ አድርሱልኝ ማለት የተለመደ በመሆኑ “ትንሽ ብር ተከፍሏቸው” ማድረስ የነበረ አሰራር ነው ትላለች።

በተለይም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሽሮ፣ በርበሬና ሌሎችንም እቃዎች ይዘው መሄድ የተለመደ ቢሆንም ነገር ግን ስዕሎች ከዚህ በፊት ወስዳ እንደማታውቅ ትናገራለች ። “ከግለሰቧ ጋር በስልክ በምታወራበት ጊዜ አምናታለች ። እንዲህ አይነት ነገር ደግሞ በፍፁም አልመጣላትም፤ ያሰበችው አይመስለኝም” በማለት ታስረዳለች።

ከዚህ ቀደም የነበራትን ልምድ በማስታወስ “ፈሪ ናት” ትላለች። ጓደኞቿንም ሆነ የሥራ ባልደረቦቿን ዕቃ እንዳይወስዱም እንደምትከለክል ጠቁማለች። “ልብስ ወይ አንዳንድ ነገር ካልሆነ ከሌላ አገር ይዛ አትመጣም ከዚህም ይዛ አትሄድም” ስትል ታስረዳለች።

ቤተሰቦቿ ኢትዮጵያ ውስጥ ደወለችላት የተባለችውን ሴት ድምፅ ከኢትዮ ቴሌኮም ለማስወጣት እንዲሁም የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮም በመሄድ ስለ ግለሰቧ ዘርዘር ያለ መረጃ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።

ሰላማዊት እጅጉ

የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮው ብዙ ተስፋ የለውም እንዳሏቸው የምትገልፀው ቤተልሔም “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች መክሰስ ፈልገን ነበር። እዚህ ያሉት ሰዎች እስር ብዙ ጥቅም እንደሌለውና እዛ ያለውን ማጠናከር እንደሚገባም ነግረውናል” ትላለች።

ሆኖም አሁንም የግለሰቦቹን ማንነት ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቃለች። በወቅቱ የአንድ አመት ከሰባት ወር ልጃቸውን እያባበለ የነበረው ባለቤቷ ከዚህ ቀደም በራይድ ስትሄድ ለጥንቃቄ ሲባል የታርጋ ቁጥሮችን ይመዘግብ የነበረ ቢሆንም በዚህኛው ወቅት ግን ልጃቸው እያለቀሰ ስለነበር የታርጋ ቁጥር ሙሉ ማየት እንዳልቻለም ቤተልሔም ታስረዳለች።

በአሁኑ ወቅት ጠበቃ ቀጥረው ጉዳዩን እየተከታተሉ ሲሆን ጡት የሚጠባ ህፃን ልጅ ስላላት የፍርድ ሂደቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆንና ህፃኑን የምታይበትን ሁኔታ እንዲመቻችም እየጠየቁ ነው። ጠበቃቸው 7 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉም ተነግሯቸው እሱንም በአንድ ቤተሰብ አቅም የሚቻል ባለመሆኑ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እየሰሩ ነው።

“በሂደት ሁሉም እውነት መውጣቱ አይቀርም ነገር ግን ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ መጥታ የፍርድ ሂደቷ ቢታይና ልጇን ማየት ብትችል ጥሩ ነበር” ትላለች።

የእስሯ ሁኔታ “አጠቃላይ ቤተሰቡን አመሰቃቅሎታል” የምትለው ቤተልሔም እናቷ በልጃቸው እስር ምክንያት ደማቸው ከፍ እንዳለና ልጇም በለቅሶ፣ አጠቃላይ ቤተሰቡም በኃዘን ላይ ይገኛል ትላለች።

ሰላም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሪካል ምህንድስና አራት አመት ተምራ መጨረሻ አመት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተቀላቀለች። በበረራ አስተናጋጅነትም ለሰባት አመታት ያህል ሰርታለች።

የኢትዮጵያ ቆንስላና ኤምባሲ ጥረት

ሰላማዊት በኢስታንቡል አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሏ ሲሰማ በኢስታንቡል የሚገኘው ቆንስላ ወደ ሃገሯ እንዲመልሷት (ዲፖርት እንዲያደርጓት) የአየር ማረፊያ ፀጥታ ኃይሎችን መጠየቁን እንዲሁም ድርድር ለማድረግም በርካታ ጥረት ማድረጉን አቶ ወንድሙ ያስረዳሉ።

ቆንስላውም በራሱ የኮኬይኑን መነሻ ለማግኘት በሚል፣ ግለሰቧ ተመልሳ የሰጧትን ሰዎች እንድትጠቁም ለማድረግ እንድትመለስ ቢደራደሩም ነገር ግን የአየር ማረፊያው የፀጥታ ኃይሎች “ወንጀሉ የተፈፀመው በክልላችን ስለሆነ ወደ ኋላ የምንመልስበት ምንም ምክንያት የለም” የሚል መልስ ሰጥተዋቸዋል።

አንካራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ወደ ሃገሯ እንድትመለስ የጠየቁ ቢሆንም በተመሳሳይ መልኩ የተሰጣቸው ምላሽ “ወንጀሉ በተገኘበት ነው የምትዳኘው ወደ ኋላ የምትመለስበት ምንም ምክንያት የለም” የሚል ነው።

“በአገሪቷ ህግ ነው መተዳደር ያለብን እንጂ በተለየ ህግ መተዳደር የምንችለው ነገር የለም። ይኼንን ከመቀበል ውጭ ምንም ሌላ አቅም የለንም” ይላሉ አቶ ወንድሙ።

ከዚህ በተጨማሪ “ቱርክ ከኮኬይን ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ስላለ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ ወንጀል አይደለም። በጣም ጠንካራ ቁጥጥር ነው የሚያደርጉት። ሰላምን ወደ ሃገሯ ትመለስ ብለው በመጠየቃቸው ብዙም ደስተኛ አልነበሩም” በማለት ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት የሰላምን ደህንነት በጥብቅ እየተከታተሉ እንደሚገኙና እርሷንም በአካል ለመጎብኘት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። በአለም አቀፉ አሰራር መሰረት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ፈቃድ ሲገኝ እስረኛ መጎብኘት እንደሚቻል ይናገራሉ።

በኮቪድ-19 ጥብቅ መመሪያ መሰረት እስረኞችን መጎብኘት ስለማይቻል፣ በቁጥጥር ስር ከዋለችበት ዕለት ጀምሮ በአካል አይተዋት አያውቁም። አቶ ወንድሙ ሲፈቅድላቸው የእስር ሁኔታ ዝርዝሩን እንደሚረዱ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢንስታንቡል ከተማ እስር ቤት የምትገኝ ሲሆን አቃቤ ህግ ክስ እስኪመስርት እየተጠበቀ ይገኛል። ቆንስላው የሚያውቀው ቱርካዊ የህግ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት የሚለውን እንዲያማክራት መጠየቃቸውንና በዚያም በኩል እየተከታተሉ እንደሚገኙ አቶ ወንድሙ ያስረዳሉ።

ከዚህ በኋላ ሰላማዊትን ለማግኘት እንዲሁም ቤተሰቦቿን በስልክ የምታገኝበትን ሁኔታ ፈቃድ እንዲኖር እየጠየቁ እንደሆነ ገልፀው፣ ጉዳዩም ወደ ፍርድ ቶሎ እንዲቀርብ ለማድረግ ግፊት የማድረግ ስራ ብቻ እንደሚሰሩ አክለው አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ሁኔታ አጋጥሞ ያውቃል በማለት ቢቢሲ አቶ ወንድሙን የጠየቃቸው ሲሆን እሳቸውም ኮኬይን የመጀመሪያ ቢሆንም በጫት ምክንያት ሶስት ሰዎች መያዛቸውን ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በቱርክም ሆነ በውጭ አገራት የማይፈቀዱ ነገሮችን ይዘው እንዳይገቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደተሰራ ያስረዳሉ። በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለእስር ተዳርገዋል ይላሉ።

አቶ ወንድሙ በቻይናም ኮኬይን ይዛ በመገኘቷ የቻይና መንግሥት ያሰራት ናዝራዊት አበራ ጉዳይን በመጥቀስ “ሰዎች የማያውቁትን እቃ እንዴት ይወስዳሉ?” በማለት ይጠይቃሉ። “የስዕል ፍሬም ውስጥ ነው ኮኬይን አድርገው የሰጧት። ለአንዱ የሚነገረው ነገር ለሌሎቻችንም ትምህርት መሆን አለበት። የተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የመደጋገፍ ባህላችን እያሉ የሚፅፉ አሉ። እሱኮ ባህል ድሮ ቀረ”በማለት በርካቶች ጥንቃቁ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ቤተሰቦቿ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስለ ሰላም እስር ሁኔታ ዝርዝር መረጃ የጠየቁ ሲሆን ሁኔታው”ኮንፊደንሻል ነው” ከማለት ውጭ ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑም ቤተልሄም ታስረዳለች።

ቢቢሲም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስለ ጉዳዩ የጠየቀ ሲሆን፣ ምላሽ እንዳገኘን ዝርዝሩን እናቀርባለን።


Exit mobile version