Site icon ETHIO12.COM

አውሮፓ ህብረት እየተሽኮረመመ ታዛቢ ሊልክ ነው

ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ መንግስትና አስተያየት የሰጡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአውሮፓ ህብረትን አውግዘዋል። ምክንያት አልባና ስሙን የማይመጥን ተቋም እንደሆነ ገልጸው አበሻቅጠውታል። በውስጥና በውጭ አገር ያሉ ዜጎች ተቋሙ የተደበቀ አጀንዳ ለማራመድ የሚሰራ ጸረ ኢትዮጵያ እንደሆነም ገልጸዋል። ከዚህ ሁሉ በሁዋላ አዲስ ዜና ተሰምቷል። ኮሚሽኑ እየተሽኮረመመ ምርጫ ለመታዘብ መከጀሉ።

የአውሮፓ ህብረት ቀደም ሲል የያዘውን አቋም በመቀየር ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎችን የመላክ ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ ዲና ሙፍቲ ናቸው ለውጭ አገር የመገናኛ ዘዴዎች ያስታወቁት።

የአዉሮፖ ህብረት ከዚህ ቀደም ታዛቢዎችን የመላኩን እቅድ አንደሰረዘ አስታውቆ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ ባለፉት ምርጫዎች ኮሚሽኑ በታዛቢነት ስም ሲታልላቸው ከነበሩት የተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ” መጣ ቀረ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም” ሲል ምን ያህል ሲያጭበረብራቸው እንደነበር ለአገር ቤት ሚዲያዎች ተናግረው ነበር። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ መሁራንና የፖለቲካ አዋቂዎች በድፍን የአውሮፓ ህብረትን አቋም ” ሉዓላዊነትን የደፈረ” ሲሉ አውግዘውታል።

የአውሮፓ ኮሚሽን የምርጫ ቦርድን ስራ ለመስራት ” ቀደሜ የምርጫ ውጤት ላውጅ፣ ለዚህም ይረዳኝ ዘንዳ የቪያሳት ሳተላይት ይዤ ልግባ” ሲል ላቀረበው ጥያቄ፣ መንግት ” ወግዱ፣ ይህ ሉዓላዊነትን መጋፋትና የአገሪቱን ህግ መጣስ ነው ” ማለቱ በዜጎችና በምሁራን ዘንድ አግባብ እንደሆነ ምስክርነት ሲሰጥበት ሰንብቶ ነበር። በተለይም ህወሃት እንዳሻው የሚመራው የምርጫ ቦርድ ተክሎ መቶ ከመቶ ምርጫ እንዳሸነፈ ሲሳውጅ በአጃቢነት ሲሰራ የነበረ ተቋም፣ ቢያንስ ለምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ንቀት ምሳየቱ ፍላጎቱ ሌላ እንደሆነ የሚያሳብቅ፣ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚሰራውን ደባ የሚያግዝ እንደሆነ ፕሮፌሰር አልማርያም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬ ዕለት ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ባለሙያዎችን ለመላክ መዘጋጀቱን እንዳሳወቀ ይፋ አድርገዋል። ቃለ አቀባዩ ኮሚሽኑ ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በምን አግባብ እንደተወ ግን ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም። ኮሚሽኑ ምርጫ አልታዘብም ያለበትን ምክንያት ኢትዮጵያ ሕዝብ በገሃድ እንዲያሳውቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህብረት ላቀረበው ጥያቄ መልስ ስለመስጠቱም የተገለጸ ነገር የለም።

የ6ኛው ብሔራዊ አቀፍ ምርጫን አስመለክቶ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየዉ የምርጫ ሂደቱ በተሞላ መልኩ እየተካሄደ ነው። ምርጫውን ለመታዘብ ጥያቄ ያቀረቡ የሀገር ዉስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫዉን ለመታዘብ ዝግጅታቸዉን አጠናቀዋል። ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ምርጫ የመታዘብ ሂደቱም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በኩል የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የሚፈጸም መሆኑን  ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በምክንያታዊነትና በፍትሃዊነት በጋራ የመጠቀም መብት አክብራ እየሰራች እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል። ከአባይ ውሃ 86 ከመቶ በላይ የምታመነጭ ሀገር በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች አሁንም ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የመጠቀም ተግባር ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን ኢትዮጵያ ስትገልጽ መቆየቷን አስታውሰዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኛዉ ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አምባሳደር ዲና እንደወትሮው ደግመው ገልጸዋል። አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የዉሃ ሙሌት ጀምሮ መረጃ ለመለዋወጥ ያላትን ፍቃደኛነት በገሃድ እንዳሳየች፣ ዛሬም በዛው አቋሟ ጸንታ እንዳለች ገልጸዋል። በዚሁ የማይታጠፍ መረሃ መሰረት ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ባለሙያዎችን በመሰየም የሁለተኛው ዙር የግድቡን የዉሃ ሙሌትን በተመለከተ አስፈላጊው መረጃ መለዋወጥ እንዲቻል ያላትን ፍላጎት ማሳየቷንና ግብዣ መላኳን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለዉ መርህ በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሶስትዮሽ ድረድሩ እንዲቀጥል ያላትን ፍላጓት በተለያየ መንገዶች እየገለጸች መሆኑን ጠቅሰዋል። በሱዳንና ግብፅ በኩል ግን ጉዳዩ አለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረዉ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ኢትዮጵያ ከምትከተለዉ መርህ ዉጭ መሆኑን አመልክተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በታዘቢነት የሚሳተፉ አካላት ሚና ማሳደግን በተመለከተም ቀደም ሲል ታዛቢዎች የድርድር ሂደቱን ከመታዘብ ውጭ ሌላ ሚና እንዳልነበራቸው ገልጸው፣ በዲሞክራቲ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሊቀ-መንበርነት በተደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ወቅት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ግን ታዛቢዎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ እንዲሁም ከተደራዳሪ ሀገራት ጋር በተናጠል ሀሳብ እንዲለዋወጡ የሚፈቅዳላቸው  ስለመሆኑ አብራርተዋል። አክለውም ግድቡ ግንባታ ሂደት እና ሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ረጅም ዘመን የተሻገር መሆኑን አንስተው፣ የሀገራቱን ድንበር በተመለከተም በመሪዎች እንዲሁም በጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ደረጃ በተለያየ ጊዜ ውይይቶች ሲያደርጉ መቆየታቸዉን አስታዉሰዋል።

ሱዳን በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተከናወነው የህግ ማስከበር ዘመቻን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ልዑላዊ ግዛትን በመውረር የቁስ እና ሰብዓዊ ሀብት ውድመት መፈጸሟን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በሱዳን በኩል በግድቡ ዙሪያ እና በድንበር ጉዳይ የሚነሳዉ ጥያቄ የሚያመለክተዉ የሶስተኛ ወገን ፍላጎት ያለበት መሆኑን እንደሆነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራች መሆኑን አስታዉቀዋል።


Exit mobile version