ETHIO12.COM

” አሸባሪዋ” ሱዳን በፓሪስ ስትሞሸር – ኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክ ማምረት እንደሚጀምር አወጀች

ህወሃት በአሜሪካ የአሸባሪነት መዝገብ ዛሬም ደርስ ተመዝግቦ እያለ አሜሪካ ወገቧን ይዛ ሌሎችን በማስከተለ ዳግም ነብስ ልትዘውራለት እየተሯሯጠች ባለበት፣ ከአሸባሪነት መዝገብ ስሟ ተሰርዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የባለጠጎቹን ቀልብ የሳበችው ሱዳን በፓሪስ እየተሞሸረች ባለችበት ወቅት ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የማምረት ስራውን እንደሚጀመር ይፋ አድርጋለች።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ የ50 ቢሊዮን እዳ ስረዛ ያወጀላት ሱዳን ምን ተገኝቶና ምን ታስቦ በፓሪስ በዚህ ደረጃ ለትሞሸር እንደቻለች እስካሁን ሚስጢሩን የገለጹ የሉም። በተመሳሳይ ኢትዮጵያን እኒሁ ባለጸጋ የሚባሉት የዓለም አውራዎች ነክሰው የያዙበት ሚስጥረ ማተብ ከመላምት ባለፈ ዘርዝሮ የሚያቀርብ ወገን አልተገኘም። ይሁን እንጂ እኒህ ባለጸጋና ” እንደልቡ” የሚባሉት አገሮች በየቦታው ከሚፈጽሙትና እይፈጸሙ ካሉት ጭካኔ የተሞላው ጭፍጨፋ አንጻር ለትግራይ ሕዝብ አዝነው እንዳልሆነ በርካታ አስተያየት ይሰጣል። ለምን ቢሉ የሚያዝን ህሊናም ሆነ ልቡና የላቸውምና።

በፓሪስ ለተሞሸረችው ሱዳን የፈረንሳዩ መሪ ማርኮ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ ካደረጉ በሁዋላ የትላንቷን የዘመናት” አሸባሪ ” አገር ሱዳንን ” “Sudan can be a model for Africa and the Arab world” ለአፍሪካና ለአረቡ ዓለማት ምሳሌ ትሆናለች ሲሉ አቆለጳጵሰዋታል። በአልበሽር ጊዜ ተቆልፎባት የነበረችው ሱዳን የክፉ ጊዜ ወዳጇን ሩሲያን ከፓሪስ ንግስናዋ በፊት ” ከባህር ክልሌ ነቅለሽ ውጪ” በማለት ታዝዥነቷን እንዳጽናች አስታውቃም ነበር።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክልል 60 ኪሎሜትር ጥሳ የያዘችን አገር በአደባባይ የሚያወድሱና በዶላር እያጠመቁ ያሉት አገራትና ተቋማቸው አይ ኤም ኤፍ ቆይቶ ሱዳን ላይ ምን እንደሚተክል የሚታይ ቢሆንም ለኢትዮጵያዊያን ታላቅ መልዕክት ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ሩጫው ኢትዮጵያን ምን ለማድረግ እንደሆነ በማስላት ተናቦ መንቀሳቀስ ሲገባ እነዚሁ ስያውቁ ለሳንቲም ለቀማ፣ እያወቁ በክፍያ፣ ሆን ብለው ለስልጣን የክፋት ወጥመድ ለደገሱት አካላት በሚተቅም መልኩ እየሰሩ ያሉ ” ዜጎች” መኖራቸው በርካቶችን እያሳዘነ ነው። እነዚህ ጥቂት ወገኖች ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ላይ ከፈጠረው ሃይልና አንድነት በታች መሆናቸው በጀ እንጂ አካሄዳቸው አገር የሚሰብር ለመሆኑ ጥርጥር እንደሌለው በየአቅጣጫው አገራዊ ዘመቻ ያስጀመሩ እየገለጹ ነው።

ምርጫ ማካሄድና የግድቡን ወሃ መሙላት ቁልፍ ተግትባር መሆናቸውን ባለሙያዎችና መንግስት በይፋ እንደ ስትራቴጂ የተቀመጡና የሚጠየቀው ሁሉ ዋጋ የሚከፈልባቸው የኢትዮጵያ መጪ እድል የሚወስኑ ተግባራት ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ሚዲያዎች በዘመቻ የሚሰራጨውን አፍራሽ ሪፖርት በመለቃቀም ምርጫውን ከወዲሁ የማይታመን ሊሆን እንደሚችል እየጻፉ ነው። በሳእሳት የተፈተኑትን ወይዘሪት ብርቱካንም ያለ በቂ መረጃ እንዲሁ የክፉዎቹን መረጃና የዘመቻ ሪፖርት በመገጣጠም እየነካኩ ይገኛሉ።

ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግስት የታላቁ ህዳሴን ግድብ ጉዳይ አጥብቆ በመያዝ፣ የምርጫውን ስኬት ለማሳየት እየሰራ መሆኑንን አስታውቋል። የህዳሴው ግድብ እንደተባለው የሙከራ ምርቱን በክረምት ይጀመራል። የውሃ ሙሌቱንም የሚያስቆም ሃይል እንደሌለ ለህዝብ በድጋሚ አረጋግጧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ጋር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተወያየበት ወቅት እንደተገለጸው ግድቡ በክረምቱ የቅድመ ምርት እንደሚጀመር የተገለጸ ታውቋል። ለዚህም ተግባር የሚረዳው የ650 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል። በክረምት 18 ነጥብ 4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝም በመድረኩ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ወቅቱን ጠብቆ እንደሚከናወንም ነው የተገለጸው፡፡

አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የሲቪል ስራው 91 ነጥብ 8 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል 54 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም ሃይድሮሊክ ስትራክቸር 55 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን በውይይቱ ላይ መንግስት አስታውቋል። የግድቡ መጠናቀቅም የሃገሪቱን የኢነርጅ ሃይል በሰአት ከ73 ኪሎ ዋት ወደ 220 ኪሎ ዋት ያሸጋግረዋል።

የግድቡን የሙሌት ሂደት ለማደቀናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችን፣ የኦፕሬሽን እና የውሃ አለቃቀቅ ሂደቶችን ኢትዮጵያ ፈጽሞ እንደማትቀበልም፣ በዚህ ረገድ መለሳለስ ብሎ ነገር እንደሌለ ተመልክቷል። በውይይቱ የተጋበዙት የሃይማኖትና የሲቪክ ማህበራቱም ለግድቡ እውን መሆን የበኩላቸው ሁሉ እንደሚያደርጉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

“ኢትዮጵያ በከብሯ እና በነፃነቷ ፍፁም የማትደራደር ሀገር መሆኗን ሁሉም ሊገነበዘ ይገባል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ሳምንት መርሐ-ግብር በይፋ ሲያስጀምሩ መናገራቸው ይታወሳል።


Exit mobile version