Site icon ETHIO12.COM

« በሽብርተኝነት የተሰማራውን የዚህን ኃይል እጅ መቁረጥ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ የሚያሰጥ…»

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለማውገዝ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች፡-

• የአገራችሁን ሉዓላዊነት ላለማስደፈር፤ የባንዳዎችን ሴራ ለማክሸፍ እዚህ የተገኛችሁ ወጣቶችን አመሰግናለሁ

• በኮቪድ ምክንያት ሁሉም ወጣቶች እዚህ ባትገኙም በያላችሁበት ሁናችሁ ድጋፋችሁን እንደምትሰጡን እንተማመናለን

• ኢትዮጵያ የሁላችን የኩራት ምንጭ ናት፤ በአድዋ፣ በካራማራ እና ሌሎችም አውደ ውጊያዎች ጠላቶቿን አሳፍራ በመመለስ ብሄራዊ ክብሯን ሳታስደፍር የቆየች አገር እንደሆነች ታሪክ ራሱ ምስከር ነው

• ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የማይደራደሩ ቆራጦች እንደሆኑ አባቶቻችን ለዓለም እንዳሳዩ ሁሉ እኛም የነሱ ልጆች የነሱን ፈለግ ተከትለን የተቃጣብንን ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል

• አብዛኛው ህዝቧ በድህነት ላይ የሚገኝባት አገራችን ይህን ድህነት ለማስወገድና ራሷን ለመለወጥ ጥረት በማድረግ ላይ ብትገኝም የእርሷ መለወጥ ያላስደሰታችው ጠላቶቻችን ሴራ እየጎነጎኑ ጥረታችንን ለማክሸፍ እየተረባረቡ ይገኛሉ

• የማደግ ሕልማችን እንዲጨነግፍ ባንዳዎችም ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ሊጎዱን በመፍጨርጨር ላይ ናቸው

• እኛ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ሰላማችንን የመጠበቅ ሃላፊነት የኛ የራሳችን ነው

• እኛ ኢትዮጵያውያን የውሃ ሃብታችንን በፍትሃዊነት ከመጠቀም የሚያግደን ምድራዊ ሃይል የለም

• አሸባሪው የህውሃት ቡድን የሰሜን እዝ ሰራዊታችንን በማጥቃት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል፤ በዚህም ምክንያት መንግስት በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ አካሂዷል፤ መንግሥት በዚህ እርምጃው ሊደገፍ ሲገባው እየተወቀሰ ይገኛል

• የአሜሪካ መንግስት የጣለውን የቪዛ ክልከላ ዳግም እንዲያጤነው እንጠይቃለን

• ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች፤ ያላትን ሀብት ለመጠቀም ሌት ተቀን እየታተረች ነው

• እኛ ኢትዮጵያውያን ማንንም ለመበደል እንደማንሻው ሁሉ ማንም እንዲጎዳን እና እንዲበድለን የማንፈቅድ ህዝቦች ነን

• ታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ከድህነት የመውጣት ጉዟችንን ለማደናቀፍ ከተቻላቸውም ለማስቆም፣ ህዝባችንን ለረሀብ ለመዳረግ፣ የማደግ ሕልማችንን ለማጨናገፍ ሌት ተቀን ሲታትሩ ይታያሉ

• የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ለህዝባችን እራት እና መብራት እንዳይሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ እና ያልሸረቡት ሴራ የለም

• የናይል ወንዝ አብዛኛው የውሃ ድርሻ የእኛ ቢሆንም በፍትሃዊነት እንጂ ሌሎችን ጎድቶ የመጠቀም ሃሳብ እንደሌለን ራሳቸው ከሳሾቻችንም ያውቁታል

• ዛሬም ሆነ ወደፊት አባይን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም፤ ሌሎችን መጉዳት ግን አንፈልግም

• የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት በዋነኛነት የመንግስቷ እና የህዝቦቿ ነው

• አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሀገራችን ክብር እና ሞገስ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ አስቦ እና አቅዶ አሰቃቂ ጥቃት ፈፅሟል፤ በማይካድራ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ ዘግናኝ ጭፈጨፋ አድርሷል፤ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት፣ እልቂት አና መፈናቀል እንዲፈጠር መሪ ተዋናይ ሆኖ ተንቀሳቅሷል፣ ፈጽሟል፣ አስፈጽሟል

• መንግስት በዚህ የጥፋት ኃይል ላይ የወሰደው የሕግ የማስከበር እርምጃ ፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ ጭምር ነው

• በሽብርተኝነት የተሰማራውን የዚህን ኃይል እጅ መቁረጥ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ የሚያሰጥ እንጂ በምንም መመዘኛ የሚነቀፍ እና የሚወገዝ ሊሆን አይችልም

• አሜሪካ እና አጋሮቿ የዚህን ኃይል የጥፋት ተግባር በቅጡ ሳይረዱ በውስጣዊ ጉዳያችን ጭምር ጣልቃ በመግባት የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ እና የጣሉት የጉዞ እገዳ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ቆም ብለው በማስተዋል ሊያርሙት እና ሊያስተካክሉት ይገባል

• ከአባቶቻችሁ የወረሳችሁትን የአይበገሬነት ወኔ ተላብሳችሁ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ማየት የየሚመኟት ሁሌም የተዳከመች ሀገር መቼም እንደማትኖረን በማሳየት የዘመናችሁን አድዋ በደማቅ ብእር እንደምትከትቡ ሙሉ እምነት አለኝ

• ብሔራዊ ምርጫችን እነሱ ሲፈቅዱልን የምናካሂደው፣ ሳይፈቅዱልን የምንተወው ሳይሆን የራሳችን የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ፤ ይልቁንም ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ እንዲሆን የጀመራችሁትን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ አጠናክራችሁ ቀጥሉ

• እያንዳንዳችን በመካከላችን ያለውን ጥቃቅን ልዩነት እና ጥርጣሬ ከውስጣችን አስወግደን፣ ዋናው መዋጊያ መሳሪያችን ኢትዮጵያዊ አንድነታችን መሆኑን ተረድተን፣ ይህን ወሳኝ ምእራፍ በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ታላቅነት የምናስቀጥል ትውልድ መሆናችንን ለዓለም እናሳይ

Exit mobile version