ETHIO12.COM

ከወለድ ነጻ -ዘምዘም ባንክ ስራ ጀመረ በስድስት ወር ውስጥ 500 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል እንዲያስመዘግብ ስድስት ወር ተሰጠው

ወይዘሮ መሊካ

መንግሥት የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነትን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተናገሩ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ በምስረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዲያስመዝግቡ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ ስራ መጀመርን አስመልክቶ አቶ አህመድ ሺዴ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነት ለማስፋት በመሰራት ላይ ነው ብለዋል።

በዚህም ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለውጡን ተከትሎ በተካሄዱት ሪፎርሞችና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት አመራር ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።የሙስሊም ማህበረሰብ ሲያነሳው የነበረው በባንኩ ምስረታ ምላሽ ማግኘቱን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

ባንኩ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የባንኮች አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያላቸው በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።በዚህም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ዘርፍ ለማሳደግ ባንኮች አቅም እንዲያጎለብቱ፣ ከጎረቤት አገሮች ባንኮች ጋር ጠንካራና ተፎካካሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ገዢው አመልክዋል።

በአገሪቱ ያሉ ባንኮች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል፣ በመሰረተ ልማትና በካፒታል እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።በአገሪቱ የፋይናንስ ተደራሽነበት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በተለይ በገጠር ተደራሽነቱን ለማሻሻል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት ባንኮች በአቅምም ሆነ በብዛት ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወለድ ነጻ ባንኮች እንዲፈጠሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ባንኩ በተለይ የፋይናንስ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች ለማደረስ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባንኩ በተለይ በእምነት ምክንያት የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እምነታቸውን መሆኑን ዶክተር ይናገር ገልጸዋል።በአገሪቱ በምስረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ የተፈቀደ ካፒታላቸው መጠን 500 ሚሊዮን ብር አድርገው እንዲመዘገቡ ገዢው አሳስበዋል።

ይህንን ካፒታል ካላሟሉ ግን መመስረቻ ካፒታላቸው አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ገልጸዋል።በአሁኑ ወቅት በምስረታ ላይ የሚገኙት 16 ያህል ባንኮች መስፈርቶችን በሟሟላት ወደ ሥራ እንዲገቡ ዶክተር ይናገር አስገንዝበዋል።

የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ መሊካ በድሪ እንዳሉት ባንኩ በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አስተዋጽኦ ለመወጣትና አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ ነው።በ876 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ያካሄደ ሲሆን፤ 11 ሺህ ባለ አክሲዮኖች አሉት ብለዋል።የሸሪያ ህግን የተከተለና ሁሉን አቀፍ የባንክ አገልገሎት በመስጠት በኢኮኖሚ ውስጥ ድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራም ወይዘሮ መሊካ ተናግረዋል።(ኢዜአ)


Exit mobile version