Site icon ETHIO12.COM

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561. 7 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561. 7 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ፡፡የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 97ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በወቅቱ ለበጀት ዝግጅቱ ታሳቢ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ተለዋዋጭነት እንደተጠበቁ ሆነው አሁን ለሚታዩ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት በ2013 በጀት ላይ ለውጦችን ማድረግ የሚያስገድድ ሆኖ በመገኘቱ የተጨማሪ በጀት ጥያቄና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ በጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያቶች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ህግ ለማስከበር ከተወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች ለእለት እርዳታ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል፣ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአቅም ግንባታ ፕሮጀክትና የመጠባባቂያ በጀቱ በማለቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ወጪዎች የመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

ተጨማሪ በጀቱም ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከሀገር ውስጥ ብድር እና ከልማት አጋሮች በተገኘ ብርድና እርዳታ የሚሸፈን ብር 26 ነጥብ4 ቢሊዮን ተደግፎ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በተጨማሪ በጀት አጀንዳ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለተኛ ደረጃ የተወያየው በ2014 የፌዴራል መንግስት በጀት ላይ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትና እድገት የመንግስት ኢንቨስትመንት ያደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የማክሮ ፋይናንሻል፣ የመዋቅራዊ አደረጃጀትና ቁልፍ የዘርፍ ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ፣ በተጀመሩ መንግስት የልማት ድርጅቶች ለማጠናቀቅ ጥረት በማድረግ እንዲሁም በጥናት ላይ በመመስረት የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግል በማዛወር ረገድ የተሳካ የማክሮ ኢኮኖሚ ማስተካከያዎችን ማድረግ ተችሏል ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡

የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ለመደበኛ ወጪዎች ብር 162 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203 ነጥብ 95 ቢሊዮን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 12 ቢሊዮን በጠቅላላ ድምር ብር 561 ነጥብ 67 ቢሊዮን በጀት በረቂቅ አዋጅ ተደግፎ ቀርቧል፡፡

የ2014 የፌደራል መንግስት በጀት ከ2013 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ18 ፐርሰንት ብልጫ ያለው ሲሆን የበጀት አመዳደቡም የኢትዮጵያን የብልጽግና አቅጣጫዎች መሰረት ያደረገ መሆኑን በጥልቀት በመገምገም ግብዓቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

(ኤፍ.ቢ.ሲ)


Exit mobile version