ETHIO12.COM

“እኛ ኢትዮጵያውያን ባንዳዎችን ማጥራትና ማስቆም ግዴታና ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ሥራ ነው“ ጠ/ሚ ዐቢይ

የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በምረቃው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮችን አልፎ ለምረቃ መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የተወጠነው ከ60 ዓመታት በፊት በግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መኾኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብልጽግና ፈተና ከውስጥም ከውጪም በመሆኑ የፕሮጀክቱ ሥራ እንዳይሠራ ጋሬጣዎች እንደነበሩ ነው የተናገሩት፡፡

ፕሮጀክቱ ለዓመታት በመዘግቱ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያለበትን ሁኔታ በመገምገም የፕሮጀክቱ ተቋራጭ የነበረው ሜቴክ ሥራውን እንዲያቋርጥ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሥራዉን በአግባቡ እንዲያራምድ ተጨማሪ በጀት በመመደብ ለአምስት ወራት በፋብሪካው ስም የተከማቹ አላስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማንሳት ሲሠራ እንደቆየም ተናግረዋል፡፡ በ18 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅም ሲሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡ “በገባነው ቃል መሰረት ፕሮጀክቱ ለምርቃ በቅቶ ስላየነው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተስፋ ሳይሆን ሪቫን ስለምንቆርጥ እንኳን ደስ አላችሁ“ ብለዋል፡፡

የለውጡ ዋና ግብ ቃል መግባት፣ ቃል ማክበርና መፈጸም እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ከባንዳዎችም ኾነ ከባዳዎች ፈተና ይገጥማታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንዳዎች ዛሬም እንደ ጣሊያኑ ጊዜ ሀገራቸዉንና እናታቸዉን ካልሸጡ ሥራ የሠሩና የተሳካላቸው አይመስላቸውም ነው ያሉት፡፡ ባንዳዎች የኢትዮጵያ ብልጽግና ድክመቶችና ጠላቶች ተብለው እንደተለዩ ተናግረዋል፡፡ “ባዳዎች ከውጪ ኾነው ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል የሚፈልጧትና የሚቆርጧት ጠላቶች ናቸው” ብለዋል፡፡

“እኛ ኢትዮጵያውያን ባዳዎችን ከመታገላችንና ከማስቆማችን በፊት ባንዳዎችን ማጥራትና ማስቆም ግዴታና ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ሥራ ነው“ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ባንዳዎች ሲጠፉ ባዳዎችም ከእኩይ ተግባራቸው እንደሚቆጠቡ ነው ዶክተር ዐቢይ ያስረዱት፡፡

ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ጋር ለማስታረቅ፣ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ አሻራ ለማልበስ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ወዳጆች ችግኝ የመትከል ሥራን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል በመልዕክታቸው፡፡ ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ በገበታ ለሀገር መርኃግብር በወንጪ፣ በጎርጎራና ኮይሻ አስደናቂ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች እንደ ጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት የሚዘገዩ ሳይኾን በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቁ አስረድተዋል፡፡

“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለሱዳንና ግብጽ አይተኬ ትሩፋትን እንደሚያስገኝ ከንግግር ባለፈ ስንጨርሰው እኛም እነሱም የምንገነዘበው ይኾናል“ ብለዋል በንግግራቸው፡፡ ለኹሉም ጠቀሜታ የሚሰጠው ግድብ እንዲጠናቀቅ እስከ መጨረሻ ድጋፉ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ያልተጀመሩትም እንዲጀመሩ ሁሉም የኢትዮጵያ የብልጽግና ፍኖት እንዲሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ በትብብርና በአንድነት ሊያከናውነው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

“ትናንት ኢትዮጵያ በልጆቿ ደምና አጥንት እንደተከበረች ኹሉ ዛሬ ደግሞ በብልጽግ እና በልማት ዳግም የምትከበርና የምትወደስ ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት እንድንሠራ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ“ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ amahara mass media

ጠቅላይ ሚኒስትር / ዐቢይ አህመድ በጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት‼️

የፋብሪካው ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃ ተብሎ ሲጠበቅ ስምንት ዓመታትን ፈጅቷል፤

ለውጡ ሲመጣ የፕሮጀክቱ ግንባታ ስራው ተገምግሞ ተጨማሪ በጀት ተመድቦ ስራው ሲጀመር ያለአግባቡ በፋብሪካው ስም የተከማቹ ዕቃዎችን ማንሳት ብቻ አምስት ወራትን ወስዷል፣

በለስ ተጠናቆ ስራ ይጀምራል ሲባል እንኳን የጃዊ ህዝብ ቀርቶ ስራውን የሚመሩት ጉዳዩን የሚያምኑት አልነበረም፤ የዚህ ለውጥ ዋነኛ ግብ መጨረስ ነው፤ ቃል መግባት ፣ ቃልን ማክበርና መፈጸም ነው፣

በዚህና በሌሎች ፕሮጀክቶች ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ፈተናዎች ስንገመግም የለየነው ሁለት ሳንከዎችን ነው፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አንድም ከባንዳዎች አሊያም ከባዳዎች ሁለት ተግዳሮት ይገጥማታል፣

ከባዳዎች የሚገጥመን ፈተና እንደሙቀጫ ግልገል እናቷን ካልወቀጠች ስራ መስራት እንደማይመስላት ሁሉ ባንዳዎች ዛሬም እንደጣሊያን ጊዜ ሀገራቸውን እናታቸውን ካልሸጡ ስራ የሰሩና የተሳካላቸው የማይመስላቸው አሉ፤ ይህ አንዱ የኢትዮጵያ ብለጽግና ተግዳሮት ተደርጎ ተለይቷል፣

ሁለተኛው ባዳዎች ናቸው፤ ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል በመጥረቢያ የሚፈልጧት ናቸው፣ ባዳዎችን ከመታገላችንና ከማስቆማችን በፊት ባንዳዎችን ማጥራትና ማስቆም ግዴታና ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፣

ባንዳዎች ሲጠፉ ባዳዎች መጥረቢያ ቢኖራቸውም እጀታውን ስለማያገኙ እነሱን ማራቅ ከሁላችንም ይጠበቃል፣

የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ዋነኛ ግብ ኢትዮጵያን ከራሷ፣ ከልጆቿ፣ ከባህሏ፣ ከታሪኳ ፤ ከህብረ ብሔራዊነቷ፣ ከገናናነቷ፣ ከተፈጥሮ ሀብቷ፣ ጋር ማስታረቅ ነው፤ ይህ ዕርቅና የእርቅ ጉዞ የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ነው፣

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በወንጪ በጎርጎራና በኮይሻ አስደናቂ ስራዎች ተጀምረዋል፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ሀብት ወጣባቸው ስምንት ዓመት ዘገዩ ሳንል በጊዜ አከናውነን በማስመረቅ ደስታችንን እጥፍ ድርብ እናደርገዋለን፤

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ግብፅንና ሱዳንን አይተኬ ትሩፋት የሚያመጣ መሆኑን ከንግግርና ከንድፋ ባሻገር በተግባር ስንጨርሰው እኛም እነሱም በጋራ የምንገነዘበው ይሆናል፤ ይህ መሰረቱን እንዲይዝ ህዳሴን መጨረስ ሁለት ጊዜ የምናስብበት ሳይሆን የምንፈጽመው ጉዳይ ብቻ ነው፣ ENA

Exit mobile version