Site icon ETHIO12.COM

አስሩ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ባለቤትነት ማረገጫ የታሪክ ሰነዶች

አንደኛ፤

1420ዎቹ እንደተጻፈ የሚታመነው መጽሓፈ አክሱም በግልጽ እንደሚያሰረዳን የትግራይ ግዛቶችና ወሰኖች የሚከተሉት ነበሩ፡- ተምቤን፣ ሽሬ፣ ስራዮ (Seraye) ሐማሴን፣ ቡር (Bur) ሳማ (Sama) አጋሜ፣ አምባ ሰናዕት (Amba Senait) ገራልታ (Geralta) እንደርታ እና ሰሃርት (Sahart) ናቸው:: መጽሓፈ አክሱም ‹‹Ethiopia: the Land, Its People, History and Culture›› በዮሐንስ መኮንን የተጻፈውን እና John R. Short ‹‹The World through Maps: A History of Cartography›› (ገጽ 352 ይመልከቱ) መጽሓፍት እንደዋቢነት ይጠቀሳል፡፡

ሁለተኛ፤

1634 ዓ.ም የተጻፈው የእማኑኤል በሬዳ መጽሓፍ ‹‹Tractatus tres historico-geographici (1634): A seventeenth century historical and geographical account of Tigray, Ethiopia (Aethiopistische Forschungen) 1634» እንደሚያስረዳው የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠገዴ እንዳልሆኑ ብግልጽ ሰፍሯል፡፡

ሦስተኛ፤

በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያን ጎብኝቶ የነበረው የጀምስ ብሩስ መጽሓፍም በግልጽ የሚናገረው የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠገዴ እንዳልሆኑ ያመላክታል፡፡ ‹‹Travel to discover source of the Nile Volume 3›› ገጽ 582 የሰፈረውን ማብራሪያ ልብ ይሏል፡፡

አራተኛ፤

በአጼ ዮሓንስ ዘመንም የታሪክ ማስረጃዎች የሚያስረግጡት ያንኑ ነው:: የትግራይ ደንበር ተከዜ ነው፡፡ ወልቃይትና ጠገዴ በጎንደር ስር እንደነበሩ በግልጽ ፈረንሳዊው ፕሮፌሰረ ሬክለስ ጽፎታል፡፡

አምስተኛ፤

በአጼ ቴዎድሮስ ዘመንም ወልቃይትም ሆነ ጠግዴ በትግራይ ስር አልነበሩም:: በወቅቱ ወደኢትዮጵያ የመጡ የእንግሊዛዊያኑን የጉዞ ማስታወሻዎች ያጤኗል፡፡

ስድስተኛ፤

በጣልያን ግዜም የትግራይ ወሰን በደቡብ እንዳምሆኒ፣ በደቡብ ምስራቅ አበርገሌ፣ በምዕራብ ሽሬና አዲያቦ ነበሩ እንጂ ወልቃይት ጠገዴ ዋጃ ኮረም እና መሰል ቦታዎች በትግራይ ስር አልነበሩም፡፡

ሰባተኛ፤

‹‹ወልቃይትንና ጠገዴን ወደ ጎንደር የከለሉት አጼ ኃይለሥላሴ ናቸው፡፡ ይህም በነብላታ ኃይለማርያም ረዳ መሪነት የተካሄደውን የቀዳማይ ወያኔን አብዮት ለመበቀልበስና ሕዝቡንም ለመቅጣት ነው›› የሚለው መሰረት የሌለው ማስተባበያ ነው፡፡ ከጣሊያን ወረራ በፊትም ሆነ በጣሊያን ወረረና ድህረ ጣሊያን የትግራይ ወሰን ያው ተከዜ ነበር፡፡

ስምንተኛ፤

የትህነግ መሪዎችና ከታሪክ ጋር የተፋቱ የትግራይ ምሁራን ወልቃይትን በተመለከተ ‹‹የህዝብ ቁጥርና በሚናገሩት ቋንቋ ነው ወልቃይትንና ጠግዴን ወደ ትግራይ የከለልነው›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በመሰረቱ ከሆነ የዘርና የቋንቋ ክልልን ለመጀመርያ ግዜ ኢትዮጵያ ላይ የመሰረተው ጣልያን ነው:: ጣልያን ዘርን መሰረት ያደረገ ካርታ ሲሰራ የራሱን የዘርና የቋንቋ ጥናት አድርጎ ነበር:: በዚህም መሰረት ወልቃይትና ጠገዴን ወደ ትግራይ ሳይሆን ያካለላቸው ወደ ጎንደር ነበር:: ይህ የሆነው ወልቃት ጠገዴ አማራ በመሆኑ ነው፡፡ ይሄ ታሪክ ከተፈጸመ አንድ ትውልድ እንኳን አላለፈውም:: ‹‹ጎንደሬው በጋሻው›› በሚለው የገሪማ ታፈረ መጽሓፍ ላይ እንደተመለከተው በጣሊያን ወረራ ጊዜ አርበኛ ሁነው በአካባቢው የተፋለሙት የጎንደር አርበኞች ናቸው፡፡

ዘጠነኛ፡-

በዚህ ዘመን ያሉ እውቅ ኢትዮጵያንና ቀጠናውን በተመለከተ በርካታ መጽሃፍትን ያዘጋጁ ፕሮፌሰሮች ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡ ለአብነት የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲው ክሪስቶፈር ክላፕማን ‹‹Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia›› በተሰኘ መጽሓፋቸው ላይ የትግራይ ደንበር ተከዜ እንጅ ከዛ ተሻግሮ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

አስረኛ፡-

ዛሬም ድረስ በህይወት ያሉት የአጼ ዮሓንስ የልጅ ልጅ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምም እንዳረጋገጡት ‹‹የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠግዴ አይደሉም›› ሲሉ ለእውነትና ለታሪክ ያላቸውን ከፍ ያለ ቦታ በአንደበታቸው መስክረዋል፡፡
ከዚህ በላይ የቀረቡ የታሪክ ማጣቀሻዎች በሙሉ የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጅ ከዛ ተሻግሮ እንደማያውቅ ያረጋግጣሉ፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ለዘመናት በጎንደር ክፍለ ሀገር ዳባት አውራጃ፤ ቀደም ሲል ደግሞ በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ይተዳደር የነበረ እንጅ አንድም ቀን በትግራይ ተከዜን ተሻግሮ እንደማያውቅ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

ከ1983 በፊት የወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የአማራ ርስትና ግዛት ነበሩ፡፡ “ትግሬ እንጅ ትግራይ ተከዜን ተሻግራ እንደማታውቅ” የትግራይ ተወላጆች የግንባታ ስራ፣ ለቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራ ሰርተው ለመመለስ እንጅ ለነዋሪነት ከተከዜ ምላሽ መጥተው እንደማያውቁ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ዘመን ወልቃይት-ጠገዴ በመጀመሪያ የኢህአሠ/ፓ ቀጥሎም የትህነግ ጦር ወደ ሱዳን መተላለፊያና የጦርነት ቦታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ትህነግ በሽምቅ ውጊያ በአካባቢው መንቀሳቀስ ከጀመረበት 1971/72ዓ.ም ጀምሮ በነባሩ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ህዝብ ላይ ጥቃት ሲያደርስበት ቆይቷል፡፡ ይህ ጥቃት በይበልጥ መዋቅራዊ ጉልበት ያገኘው የወልቃይት ጠገዴ ግዛት በጉልበት ወደ ትግራይ ከተጠቀለለ በኋላ ነው፡፡

ሕዝባችን በማንነቱ ብቻ ለሠላሳ ዓመታት በወያኔ አገዛዝ የዘር ማጥፋት ታውጆበት ሺህዎች በጅምላ ተገድለዋል፡፡ በርካቶች ወደ መቀሌና ወዳልታወቁ ስፍራዎች ታፍነው ተወስደው በእስር ሲማቅቁ ኑረዋል፡፡ በጥቅሉ በሠላሳ ዓመቱ የወያኔ አፓርታይዳዊ ዘመን አምስት መቶ ሺህ የሚደርስ ወገናችን ከወልቃይት ጠገዴ እንዲሰደድ ተደርጓል፡፡ ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውያንና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ወልቃይት ላይ የደረሰው ግፍና በደል እምብዛም አይታወቅም፡፡ ይህ ከወያኔ የአፈና ሥርዓት ጋር የሚያያዝ ቢሆንም፣ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ዓለም ያልሰማው የዘርማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብናል፡፡ በወያኔ ስለመበደላችን ዓለም እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡
በቀጣይ ጊዜያት በውጭና በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ስለወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታዎች መረጃዎችን እናደርሳለን፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
የወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር

Exit mobile version