Site icon ETHIO12.COM

በሶስት ጣቢአይዎች ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው ስለተገኙ ነገ ምርጫ አይካሄድባቸውም፤ አጥፊዎቹ በህግ ይጠየቃሉ

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2013 የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን የያዙ ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው በተገኙባቸው የምርጫ ክልሎች በነገው ዕለት ምርጫ የማይካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ ነገ በሚካሄደው የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭትና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ እንዳሉት በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ማንም መነካካት የማይችላቸው የምርጫ ወረቀቶችን የያዙ ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው ተገኝተዋል።

በመሆኑም በአማራ ክልል ደንቢያ የምርጫ ክልል ሰማያዊ ሳጥኑ ተከፍቶ በውስጡ የድምጽ መስጫ ወረቀት የያዘው ቡክሌት ተከፍቶ በመገኘቱ ነገር ምርጫ አይካሄድም ነው ያሉት።ችግሩ መከሰቱ ከተረጋገጠ በኋላ ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ ምርምራ እንዲደረግ ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርምራ ደብዳቤ ተጽፏል።

ከዚህም በተጨማሪ በአማራ ክልል ተሁለደሬ ምርጫ ክልል አንድ እና ሁለት በተመሳሳይ እጩ ተወዳዳሪዎች ሰማቸው መኖር አለመኖሩን አረጋግጡ ተብለናል በሚል ሰማያዊ ሳጥኑ ስለተከፈተ ድምጽ አይሰጥም ብለዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ግንደበረት የምርጫ ክልል የአስፈፃሚዎች እጥረት መኖሩን ተከትሎ ወረዳው በራሱ አስፈጻሚዎችን አሰልጥኖ ሊያሰማራ ሲል ስለተደረሰበት ምርጫው እንዲራዘም ተደርጓል በማለት ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ በነገሌ ቦረና አንድ የግል እጩ ተወዳዳሪ በግሌ ተመዝግቤ የምስክር ወረቀት እያለኝ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የእጡዎች ዝርዝር ላይ ስሜ አልተካተተም የሚል ቅሬታ በማቅረቡ ቅሬታውን ለማጣራት ሲባል ነገ ድምጽ አይሰጥበትም ብለዋል።

በአማራ ክልል መተማ የምርጫ ክልል እንዲሁ በተመሳሳይ ሰማያዊ ሳጥኖች የተነካካ ቢሆንም በምርጫ ወረቀቱ ላይ ጉዳት ስላልደረሰበት ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።በደቡብ ክልል ስቄ አንድ እና ሁለት የምርጫ ክልል በእንቅስቃሴ ወቅት ሰማያዊ ሳጥኑ ቢሰነጠቅም የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች ታዛቢዎች የጸጥታ ሃይሎች ባሉበት ጉዳት ወረቀቱ እንዳልተነካካ ስለተረጋገጠ ቦርዱ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል ብለዋል።

በመሆኑም በዝቅተኛ የመንግስት መዋቅር ስር ያሉ አካላት የምርጫ ቁሳቁሶችን በማጓጓዝና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ከማድረግ ውጭ ሳጥኑን መነካካት አይችሉም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡም ይገባል ብለዋል።ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ሳጥኑ ተቆልፎ በሚንቀሳቀስበት ወቅት መክፈት፤ መነካካት መቁረጥ ወንጀል ነው ፤ድጋሚ ምርጫ ይደረግ ቢባልም የሚያስወጣው ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ነገ ድምጽ በሚሰጥበት ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ወኪሎቻቸው የሚያጋጥማቸው ችግር ካለ ከስልክ በተጨማሪ ልናግዛቸው ዝግጁ ነን ብለዋል።ከዚህም በተጨማሪ በምርጫ ሂደት ያዩትንና ቦርዱ ማወቅ አለበት ብለው የሚያስቡትን ማሳወቅ ከፈለጉ ወይም ማስተካከያ መደረግ ይገባቸዋል የሚሏቸውና ቅሬታ ካላቸው ማቅረብ የሚችሉበት ዴስክ ተዘጋጅቷል።

Exit mobile version