Site icon ETHIO12.COM

የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በብዙ መልኩ የተሳካ ነበር — ኮሚሽኑ

የዘንድሮው ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በብዙ መልኩ የተሳካ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ድምፅ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ቀዳሚ ሪፖርትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ኮሚሽኑ ምርጫውን በሚለከት ባለ 6 ነጥብ አጀንዳ ይፋ አድርጎ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ቀን የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የሴቶችን ተሳትፎ የማሳደግ፣ ምርጫው አካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በማሳተፍና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ምን ይመስል እንደነበር በትኩረት ክትትል ማድረጉን ተናግረዋል።

በምርጫው መዳረሻ ቀናትና በድምጽ መስጫ እለት 94 ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን በ99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረው የአካባቢ አስተዳዳሮችን፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ሃይሎችና የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን ማናገራቸውን አንስተዋል።

በኮሚሽኑ ዋና ፅህፈት ቤት በነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ ሲቀበሉ እንደነበርም እንዲሁ።

ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት ከመታየቱ በስተቀር በአብዛኛው ቦታዎች የጎላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመከሰቱን ገልፀዋል።

የምርጫው ዕለት የጎላ ችግር ሳይከሰት በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀበትና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንደነበርም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በአንፃሩ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው ዕለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው ዕለትና ከድምፅ መስጫ ቀን በኋላ በታጣቂዎች የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መድረሱን አንስተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ መጉላላትና ማዋከብ መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል።

የምርጫ ሂደቱ ለአካል ጉዳተኞች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ተሳትፎ የሚለከቱ ጉዳዮች በቀጣይ መስተካከል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፤ የምርጫው ቀጣይ ስራዎች ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ጥፋተኛ የሆኑ ሰዎች በአፋጣኝ ምርመራ ተደርጎባቸው ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል።

ኢዜአ

Exit mobile version