Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ሕወሓት መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርሰው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማወናበድ ትርፍ ለማግኘት ነው – ትዴፓ

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርሰው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማወናበድ ትርፍ ለማግኘት ነው – የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

ሰኔ 25/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርሰው ከሚፈጽመው ድርጊት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማወናበድ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ ነው” ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለጸ።

ሕወሓት በአሁኑ ሰአት “የትግራይ ሕዝብ ወደ ጦርነት እንዲገባ እየቀሰቀሰ” እንደሆነና ለዚህም ሀሰት እየፈበረኩ የተሳሳተ መረጃ እንዲያሰራጩለት በቀጠራቸው የተለመዱ ግለሰቦች ጥረቱን መቀጠሉ ተጠቅሷል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉብርሃን ኃይሌ “ሕወሓት አገርን የማተራመስና የማፍረስ እኩይ ተግባር እያከናወነ መሆኑንና የተከዜን ድልድይ ጨምሮ በፌዴራል መንግስትና በክልሉ ህዝብ ሀብት የተገነቡትን መሰረተ ልማቶች በማውደም ላይ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዋጋ በማስከፍል ወደ በለጠ ችግርና ሰቆቃ እየከተተው በመሆኑ የዓለም ማህበረሰብ ጉዳዩን በአግባቡ መረዳት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በፖለቲካና በጦርነት የተሸነፈው ሕወሓት የትግራይን ህዝብ ጥያቄ የመመለስም ሆነ የማስተዳደር አቅም እንደሌለው አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ “መሰረተ ልማቶችን በተለይም ድልድይ በማፈራረስ ትርፍ ለማግኘት እየሞከረ ነው” ብለዋል ።

ሕወሓት መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርስበት ለሁለት ዓላማ ነው ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስና ህዝብ የሚያቀርቡትን እርዳታ ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርስ በማድረግ “በረሃብ ሊጨርስህ ወስኗል” በሚል ፕሮፓጋንዳ ወደ ራሱ ለማሳለፍ አልሞ መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለተኛው ደግሞ ለዓለም ማህበረሰብ ድልድዮች ስለተሰበሩ ወደ “ትግራይ እርዳታ መግባት አይችልም” በሚል ምክንያት፤ “እርዳታ በአውሮፕላን እንዲገባ በመጠየቅ የሚፈልጋቸውን መሳሪያዎች በማስገባት” የጀመረውን አገር የማፍረስ ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና ፓርቲያቸው ይሄን የሚያስደግፍ መረጃ አግኝቷል በማለት ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ”ትግራይ ወጣቶች እየተሰደዱ” መሆናቸውን፤ “ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ወጣቶችን የብልጽግና፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አረና አባላት ናቸው” እያለ እያሰቃየ ነው ብለዋል።

“ሕወሓት ትግራይን ማስተዳደር አይችልም ኮሩ ፈርሳል የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ አይችልም” በዚህም በፍጥነት አመጽ እንደሚነሳበት ስለሚያውቅ “ሕዝቡን ወደ ጦርነት ለመክተት እየሰራ ይገኛል ” ነው ያሉት አቶ ሙሉ ብርሃን።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሕወሓት በአውሮፕላን እርዳታ ይቅረብ በሚል ሰበብ የጦር መሳሪያ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ እቅድ በሚል ያቀረበው ሀሳብ ኢዜአ ማስረጃ ከምንጮቹ አግኝቷል።

በአሁኑ ሰዓት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ የሚደርስባቸውን መጋቢ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ጉዳት በማድረስ እርዳታ በየብስ ትራንስፖርት እንዳይገባ መስተጓጎል እየፈጸመ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ አልደረሰም ሕዝቡ በረሃብ ሊሞት ነው በሚል ሰበብ በአውሮፓላን እርዳታ ይላክ በሚል በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ዓለም አቀፍ ጫና በማሳደር በእርዳታ ሽፋን የጦር መሳሪያ ለማስገባት ጥረት የማድረግ እቅድ እንዳለው ነው ምንጮቹ የገለጹት።

ሕወሓት “በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ የሚያደርጉለትን ማርቲን ፕላውት፣ጄቲል ትሮንቮል፣አሌክስ ዴ ዋል፡ዊሊያም ዳቪሰን፣ራሺድ አብዲ፣አወል አሎና ሌሎች ቅጥረኞቹን በመጠቀም ዘመቻ መከፈቱን ነው” መረጃዎች የሚያመላክቱት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።

Exit mobile version