Site icon ETHIO12.COM

የመከላከያ ሰራዊት ትግራይን መልቀቅ የጀመረው ከወር በፊት ነው

መንግስት በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ተሰማርቶ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ማስወጣት የጀመረው በድንገት ሳይሆን ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በትግራይ ስለነበረው የህግ ማስከበር ሂደት እና ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ ስለወጣበት ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማብራሪያቸው ሰራዊቱን ከትግራይ ለማስወጣት የተወሰነው ታስቦበት እና ተመክሮበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“አራት የተለያዩ የመከላከያ ኃይሎችን በአራት ዙር ለማስወጣት ጥረት ሲደረግ በጁንታው ቀሪ ኃይሎች የተለያዩ ትንኮሳዎች ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፤ የመጨረሻው ኃይል ከመቐለ ከወጣ እስከ ሁለት ቀን ድረስ አንድም የጁንታው ኃይል መቐለ ከተማ አልገባም ነበር” ብለዋል፡፡

ጁንታው እና ከጀርባው የተሰለፉ ኃይሎች በነዙት ፕሮፖጋንዳ ሰራዊቱ የከፈለውን መስዋዕትነት የማንኮሰስ ተግባር ተግዳሮት ሆኖ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ በህግ ማስከበር ሂደቱ የተፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶችን በመጠቀም፣ የጁንታው ኃይል ንፁሃን በመምሰል ጥቃት በማድረስ በህዝብ ላይ ሰራዊቱ አጸፋ እንዲወስድ በማድረግ እና በመሰል እኩይ ተግባራት ተልዕኮውን የማጠልሸት ስራ ሲሰሩ እንደነበር መንግስት በአግባቡ መገምገሙን ገልጿል፡፡

መንግስት በግምገማዎቹ እነዚህን አዝማሚያዎች በማየት እና የአለምን ተሞክሮ በማጤን በተራዘመ ጦርነት የደቀቀች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተያዘውን አሻጥር ለማክሸፍ የሚያስችል ውሳኔ ለመወሰን እንደተገደደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በግጭቱ ሂደት ትግራይ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን አንዳንድ ኃይሎች የሚጮሁበትን አቅም በማየት በቤንሻንጉል እና ሌሎች አካባቢዎች የሚከሰቱ ሁነቶች ሲገመገሙ የጣልቃ ገቦቹ አቋምና ፍላጎትን ለይቶ ማየት እንደተቻለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

ውሳኔው የእነ ዩክሬን፣ ኮሪያና ሌሎች አገራትን ተመሳሳይ ችግሮች በማጤን የተራዘመ ግጭት እንዲኖር የሚፈልጉ አካላትን እቅድ ለማክሸፍ ያለመ ውሳኔ ማሳለፉን መንግስት አስታውቋል፡፡

“መንግስት መቀየር አለበት ብለው የሚንቀሳቀሱ አሀገራት እንዳሉ እንረዳለን፤ ህዝብ ይሁንታውን እንደሰጠ እንኳን እነዚህ አገራት አልተገነዘቡም፤ መንግስት ለዚህ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በዋና አገራዊ ጉዳዩ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል ”ብለዋል፡፡

መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ሲያስወጣ ለህዝብ እና ለአገር ይጠቅማል በሚል ተጨማሪ ኪሳራን ለማስቀረትና መንግስት ሊሰራ ባሰባቸው ጉዳዮች ላይ ለማተኮር አስቦ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

ሰራዊቱ መውጣቱን ተከትሎ “ኢትዮጵያ ተዳክማለች” በሚል የሚነዙት አሉባልታዎች መሰረት የሌላቸው እንደሆኑ እና መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አገራዊ ተግባራ ቅድሚያ ለመስጠት እና ትግራይ አካባቢ ላለው አካልም የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ያለመ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል

Exit mobile version