Site icon ETHIO12.COM

ከመጋረጃ በስተጀርባ…

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለፌደራል መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የፌዴራል መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አውጇል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫ እንደሚያመለክተው ውሳኔው ያስፈለገበት ምክንያት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን፣ የእርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሠራጭ፣ ሰላምን የሚመርጡ የሕወሓት አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ፤ ሳያውቁ የጥፋት ኃይሉን የተከተሉ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል ነው።

ይህ የመንግስት ውሳኔ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ኃላፊነት የተስተዋለበት ስለመሆኑ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ገልጸዋል።እንደ ቻይና፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት የመሳሰሉ ሀገራት  የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔውን እንደሚደግፉ ይፋ አድርገዋል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ “አትዮጵያዊያን የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት ጥበብ እንዳላቸው እናምናለን” ሲል ገልጿል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በበኩላቸው ውሳኔው ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ በህብረቱ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ቲቦር ናዥን ጨምሮ አምስት አምባሳደሮች ውሳኔው ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ነው ብለዋል።  

ኢትዮጵያ የወሰነችው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በምእራባውያን በተለይም በአሜሪካና በአንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ዘንድ አዎንታዊ ነው በማለት የገለጹ ቢሆንም ውሳኔውን በግልጽ ሲደግፉት አልታየም። እነዚህ ሀገራት ከዚህ ቀደም የተኩስ አቁም እንዲደረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ የቆዩ ከመሆናቸውም በላይ ማዕቀብ እስከመጣል የደረሰ ተጽእኖ መፍጠራቸው ይታወቃል። ከዚህ አኳያ የመንግስት የተኩስ አቁም ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉት የብዙዎች ግምት ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ ከመሞከር አልታቀቡም። በዚህ የተነሳ ሀገራቱ ከበስተጀርባው የሚያራምዱት አጀንዳ ስለመኖሩ ብዙዎች ይጠረጥራሉ።

በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ኬንያን ጨምሮ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ መንግስት በትግራይ ክልል ለመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታና ለሰብአዊ ድጋፍ ያደረገውን ጥረት አድንቀው የተኩስ አቁም ውሳኔው ሀገሪቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚመራ እንደሆነ አብራርተዋል። በአንፃሩ አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ተወካዮች “መንግስት ያወጀው የተኩስ አቁም ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ይበልጥ ለረሃብ እንዲጋለጥ የሚያደርግ ነው” በማለት ውሳኔውን አጣጥለው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት ያልተገደብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ፍላጎት ያለው ስለመሆኑ ማረጋገጥ አለበት ብለዋል። የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ ለሕብረቱ ፓርላማ ማብራሪያ ባቀረቡበት ወቅት “ኢትዮጵያ ያወጀችው ተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው፤ ረሃብም እንደ ጦር መሳሪያ እያገለገለ ነው” በማለት ተችተዋል።

እነዚህ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡት መግለጫዎችና በሚያነሷቸው ጉዳዮች መንግስትን ከመጫን ውጪ የሕወሓት ቡድን በተመሳሳይ ተኩስ እንዲያቆም ግፊት ሲያደርጉ አልታየም። በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን የተኩስ አቁም ውሳኔውን እንደማይቀበለው ይልቁንም ለተጨማሪ ውጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን በይፋ እየተናገረ ነው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሕወሐት ቡድን ለውጊያ እየተዘጋጀ መሆኑን፤ ወጣቶችን ለዚህ ዓላማ እየመለመለ መሆኑንና በወታደራዊ እርምጃ ችግሮችን እንደሚፈታ እየገለጸ መሆኑን በተደጋጋሚ እየዘገቡ ቢሆንም ጉዳዩ በዝምታ እየታለፈ ነው።  

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ ቡድኑ በርካታ ንፁሐን ዜጎችን እያሰቃየና በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለ መሆኑ እየተነገረ እንኳ ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጡም። በቅርቡ የራያ ራዩማ ዴሞክራሴያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ጌታቸው ከበደ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሸባሪ የህወሃት ቡድን በራያና አዘቦ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን እንደገደለ መግለጻቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እንደደረሱት አመልክቷል።  

መንግስት ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እርምጃው አዎንታዊ መሆኑን ቢያመለክትም ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተለው ነበር የገለጸው። እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተዘረዘሩ ጉዳዮች መካከል መንግስት በፍጥነት የስልክና ሌሎች መሰረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲያመቻች፣ የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም የአማራ ልዩ ሀይል ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ክልል መውጣቱን እንዲያረጋግጥ፣ የእርዳታ ሰራተኞች ያለገደብ በነፃነትና ደህንነታቸው ተጠብቆ በሁሉም ቦታዎች የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ እንዲፈጥር የሚያሳስብ ነበር።

በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች የአንድ ጀምበር ሳይሆኑ ለወራት በአሜሪካና በአንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ባለስልጣናት እንዲሁም በለጋሽ ድርጅቶች በኩል ሲቀነቀን የቆየ አጀንዳ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት  በመግለጫው ላይ “—አንዳንድ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ችግሩን ለመገንዘብ ፍላጎት አላሳዩም፡፡ ለእርዳታ የከፈትንላቸውን መሥመርም ላልተገባ ተግባር ሲጠቀሙበት ታይተዋል፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎችም ከእውነት በተቃራኒ መቆምን መርጠዋል፡፡ ከሚደርሱት ርዳታዎች ከሰባ በመቶ በላይ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ እየታወቀ ለመንግሥት ተግባር ዕውቅና ነፍገዋል፡፡” በሚል መግለጹ የሚታወስ ነው።  

ከሰሞኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውንና በመንግስት በኩል መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ማሳሰባቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ድንበሮች በኃይልም ሆነ ህገ-መንግስቱን በመጣስ እንደማይለወጡ አሳስበዋል። በተጨማሪም ሁሉን አሳታፊ ለሆነ ውይይት መደላደል እንዲፈጠር፣ በድርድር ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቁ ናቸው። ይህን ተከትሎ ብዙ አስተያየት ሰጪዎች የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የያዘው አቋም ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከመፍትሔ ይልቅ ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ የሚያደርግ ነው በማለት ተችተዋል። ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ አካሄድ ነው ሲሉ ሀሳቡን ተቃውመዋል።

ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሜሪላንድ የሆነው ዶ/ር ሐይማኖት አሰፋ WHEN HAS TIGRAY BECOME A US STATE?” በሚል ርእስ በፃፉት ጽሑፍ አሜሪካ በግልጽ ከህወሃት አፍራሽ አስተሳሰብ ጋር በመቆም የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉአላዊነት እየተጋፋች  ነው ብለዋል። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተሰጠው መግለጫ እንዳስቆጣቸው የገለጹት ዶ/ር ሐይማኖት አንቶኒዮ ብሊንከን የሰጡት ማሳሰቢያ የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት በግልጽ የሚጻረር ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ነጻና ሉአላዊት ሃገር በመሆኗ ምን ማድረግ እንዳለባት ከአሜሪካ አይነገራትም የሚሉት ዶ/ር ሐይማኖት፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ደሃ ብትሆንም ነጻና ሉአላዊት ሀገር መሆኗን አሜሪካ መረዳት አለባት ነው ያሉት። የአሜሪካ የፖለቲካ ልሂቃን ከህወሃት ጋር በግልጽ መወገናቸውን ስለማሳየታቸው አመልክተው አሜሪካ ለሰብአዊነት መከበር ቢያሳስባት ኖሮ ከ100 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው ኢትዮጵያዊ ጎን በመቆም አቋሟን ትገልጽ እንደነበር አብራርተዋል። አያይዘውም አሜሪካ አሁንም ህወሃት አንሰራርቶ ስልጣን እንዲይዝ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም የሚያመለክት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማእከል ዳይሬክተር ብሮንወይን ብሩቶን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ሃሳብ የሕወሓት ቡድን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሰጠው ማሳሰቢያ ተነሳስተው በአማራ ሚሊሻ ላይ ጥቃት ቢፈጸም መላው የአማራ ሕዝብ አጸፋውን ለመመለስ መንቀሳቀሱ እንደማይቀር አመልክተው ይህ ሁኔታ ህዝብ እርስ በርሱ እንዲገዳደል የሚያደርግ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍ የሚችል ነው በማለት አስጠንቅቀዋል። 

የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሞ ፔካ “Pressure from US and EU Gives Wrong Signal: Violence Pays Off”በሚል ርእስ በፃፉት ትንታኔ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ የሚከተሉት ፖሊሲ ቀጠናውን ወደ ትርምስ እንዲገባ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተችተዋል። በተለይ በትግራይ ክልል ህግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ ሁለቱ አህጉራት ለህወሓት ከለላ ሲሰጡ ታዝበናል የሚሉት ጸሐፊው ይህ አካሄድ ቡድኑ ይበልጥ ለጥፋት እንዲነሳሳ ከማድረጉም ባሻገር ተመሳሳይ ችግር በሌሎችም አካባቢዎች እንዲከሰት በር ከፋች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያም ይሁን ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ብዙ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን የሚጠቁሙት ሲሞ ፔካ ታጣቂዎቹ የህወሓትን ዓይነት አጥፊ መንገድ እንዲከተሉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ወሳኔ ለዘላቂ ሰላምና በሀገሪቱ መረጋጋት እንዲፈጠር የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ስለመሆኑና ሊደገፍ የሚገባው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ግን አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሚያራምዱት አቋም ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ ከተቻለ የሀገርን ሉአላዊነት ያከበረ አቋም እንዲያራምዱ ካልሆነም ከህወሃት ቡድን ጋር አለመወገን ለሀገር እንደሚበጅ በርካቶች አስተያየት ይሰጣሉ።ሰላም!

አብዱራህማን ናስር /ኢዜአ/


Exit mobile version