Site icon ETHIO12.COM

አዴሃን-በአገር ጉዳይ ” ግንባር እሆናለሁ” አለ

እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በግንባር ቀደምትነት እንደሚቆም የአማራ ዴሞክራሲዊ ሃይል ንቅናቄ /አዴሃን/ አስታወቀ። ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ  በባህር ዳር ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ነው።

የድርጅቱ የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ምርጫው ስንሻው በመግለጫቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በውጭ ሃይሎች እንዲጣስ እየጣረ ይገኛል።

“በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥም ሆነ ከውጭ እየደረሰ ያለውን ፈተና አዴሃን ተገንዝቧል” ያሉት አቶ ምርጫው፣ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የአማራ ህዝብ መብትና ጥቅም የሚከበረው ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯ ታፍራና ተከብራ ስትኖር መሆኑን ገልጸው፣ “በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም ማለት ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም” ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰሜን እዝ ላይ በፈጸመው ጥቃትና አማራን በመውረር ራሱ ግጭት እንደለኮሰ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገንዝቦ ትክክለኛውን ፍትህ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ አልምታ እንዳትጠቀም፤ በሌላ በኩል በውጭና በውስጥ ሴራ ሉአላዊነቷና የህዝቦቿ ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ጥረት እየተደረገ መሆኑን  መረዳት እንደሚገባ አስረድተዋል።

“የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እኩይ ዓላማን ለመግታት አዴሃን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን የፖለቲካ ትግል በማድረግ ለሀገር ሉአላዊነት ከሚታገል  ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁኔታው በጥልቀት በመረዳት ለችግሩ የሚመጥን ዝግጅት በማድረግ ተገቢ ምላሽ መስጠት  በአንድነትና በጽናት እንዲቆሙም  መልዕክት አስተላልፈዋል።

“አማራነት የሚፈተንበት ወቅት ነው” ያሉት ሃላፊው፣ ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ግዴታቸውን  እንዲወጡም ጥሪ አቀርበዋል። “እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በግንባር ቀደምትነት መቆማችንን እንገልጻለን” ማለቱን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።


Exit mobile version