Site icon ETHIO12.COM

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኦሮሚያ ክልል የተሰጠ መግለጫ

የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያን በመገንባት ዉስጥ የሚመጥነዉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነትና ነጻነትን ለማስከበር በሚከፈለዉ መስዋእትነት ላይ ራሱን ቆጥቦ አያውቅም፡፡ በውጪ ወረራና በታሪክ አጋጣሚ የባንዳነትን ተግባር ስፈጽሙ በነበሩት ኃይሎች ላይ በየታሪክ ምዕራፉ ራሱን ሰጥቶ ኢትዮጵያን የገጠሙዋትን ችግሮች ለማክሸፍ መስዋእትነትን ከፍሏል፡፡ እንደ ሀገር ስናስመዘግብ በቆየናቸው ድሎች ውስጥ ተወራራሽ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በማቀናጀት በወንድሞቻችን አብሮነት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ የወሰደዉን የአንድ ወገን ተኩስ የማቆም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ጊዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ስደግፍ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከአፈጣጠሩ የተጣመመው ሕወኃት/ጁንታ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገው ጥሪ ቦታ እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የፖለቲካ እይታ ተሞልቶ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡ የሕወሓት የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ሕዝብን እንደ ጠላት በመፈረጅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የግጭት መነሻ የአንድነት ጸርና ለሀገራዊ ብሔርተኝነት መውደቅ ምክንያት ሆኗል፡፡

የጁንታው ጸረ አንድነት ፈንጂ በየቀኑ እየፈነዳ ለዜጎች ሞትና ስቃይ ምክንያት በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የድህነትና የኋላ ቀርነትን እሽክርክሪት ዘመን አራዝሞብናል፡፡ ለእድገታችንና የብልጽግና ጉዞ እንቅፋት በመሆን እንድንሸማቀቅ አርጎናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ በቀዳሚነት እየተጎዱ ነው፡፡ ሕወሓት/ጁንታ እታገልላቸዋለሁ ብሎ የሚናገረውና በስማቸው እየኖረ ያለዉን የትግራዋይ ሕዝብን ጨምሮ አስቦላቸዉ ወይም ተቆርቁሮላቸው አያውቅም፡፡ ይህ ቡድን ትናንት የሐውዜን ሕዝብ በሚገበያይበት ቦታ ላይ ቦምብ በማዝነብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ለፕሮፖጋንዳ ግብዓትነት እንጂ ለሉዓላዊነት ትግል አልነበረም፡፡ ሕዝብን በመጨፍጨፍ ሕዝብን ነፃ ማውጣት በየትኛውም መስፈርት የሚታረቅ አስተሳሰብ አይደለም፡፡

ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት የወጣውን የሕጻናት መብት ድንጋጌ በመጣስ ጨቅላ ሕጻናትን ለጦርነት ከፊት አሰልፈው በመማገድ ላይ ይገኛል፡፡ አዛውንቶችን፣ እናቶችንና የሃይማኖት አባቶችን እንደ ጋሻ ከፊት በማሰለፍ በእልቂታቸው የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል፡፡

አሁንም ቢሆን ሕወሓት/ጁንታ የፌደራል መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ካሳየው ፍላጎት በተቃራኒ በመሔድ ላይ ይገኛል፡፡ በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፤ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም ጁንታው የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜትና እጅ መቆጣጠር አልቻለም፡፡

የ1967ቱ የሕወሓት/ጁንታው ማኒፌስቶ ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት ሰላምና መረጋጋትን ለመንፈግ የተወጠነ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ግንባታ ቋሚና ማገር በመሆን ለዛሬ ያደረሳትን ሕዝብ ለመበታተን ያለመ ነው፡፡ ሕወሓት/ጁንታ ላለፉት 27 ዓመታት ሀገር ሲመራ በነበረበት ወቅት በሕዝብ ውስጥ ትቶት ያለፈው ሰቆቃ ሳያንስ ዛሬም በሀገር ላይ የጭካኔ ተግባራትን እየፈፀመ ነው፡፡

ሕወሓት/ጁንታ በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር በብሔር ላይ ያተኮረ የሕዝብ ጠላትነት ላይ የተመሰረተ እኩይ ተግባር ነው፡፡ አሁንም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም ሲቅበዘበዝ ይታያል፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ኃይል የሕዝብና የሀገር ጥቅምን አሳልፎ ከመስጠት አይመለስም፡፡ እድገታችንንና ልማታችንን ለመግታት ከሚታገሉ የዉስጥና ውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋትና የማፍረስ ሴራዎችን በዋና ተዋናይነት ሲፈፅም እንደነበረ በገሀድ ታይቷል፡፡ ሕወሓት/ጁንታ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል ጀምሮ ከነአካቴው እስከ ማደናቀፍ ድረስ የተላላኪነትና የባንዳነት ትወና ድርሻውን ተወጥቷል፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ክህደት በሕዝብ ንቀት ብቻ የተገታ አልነበረም፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እስከሚገባ አስነዋሪ ተግባር ፈፅሟል፡፡ ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በውጪ ወራሪ ብትወረርም ደንታ እንደሌለው እስከመግለፅ ደርሷል፡፡ ስለሆነም ሕወሓት/ጁንታ ለአንዱ የሚያስብ፣ ሌላውን የሚነፍግ ሳይሆን በጅምላ የመጨፍጨፍና የማፈራረስ አቅጣጫን ይከተላል፡፡ ከእሱ ተወልዶ፤ ከእጁ በልቶ ላደገው ሕዝብ የማይራራ፣ ሌላ ዘመድ ሊኖረውም ሆነ ሊያፈቅር አይችልም፡፡ “ጅግራ ዘመድ መስሎ ወፊቱን በላት እንደሚባለው ሁሉ፤ ለአንዱ አዝኖ፤ ሌላውን አኩርፎ ሌሎችን ደግሞ የተፀየፈ መስሎ የሚቀርበውን ፕሮፖጋንዳ አምኖ መቀበል ሞኝነት ነው፡፡

የሕወሓት/ጁንታ ኃይል ተሸንፏል፤ በፖለቲካ ሜዳዉ አሸናፊ ሐሳብ ማቅረብ ተስኖት ለቆ ስደትን መርጧል፡፡ በማግስቱ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ጀመረ ፡፡ ውሎ ሳያድር በዜጎች ላብ የተገዛውን የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት መሳሪያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዛተ፡፡ ከሀዲዎችና የውጪ ኃይሎች ማበረታቻ የሰከረው ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ለይ የጥቃት እርምጃ ወሰደ፡፡ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት በከባድ የጭነት መኪናዎች ከመጨፍለቅ ጀምሮ እጅግ አስነዋሪ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የክልልና የሀገራችን ሕዝብ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ሁሉ አቀፍ ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን ማናቸዉንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነዉ፡፡ መንግሥትም የሕዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት ሁለንተናዊ ስኬት ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡

ትናንት በችግር ውስጥ የመንግሥትን ጥሪን በመስማት ሁለንተናዊ ድርሻችሁን የተወጣችሁና የአሸባሪዎች የጥፋት መርዝ እንዲደፋ ያደረጋችሁ የክልላችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም እንደ ትናንቱ የጎላ ተሳትፏችሁን እንድታበረክቱ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በሕዝባችን የተባበረ ክንድ ዘላቂ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል!

Exit mobile version