Site icon ETHIO12.COM

«አየር ኃይል የትኛውም ኃይል ላይ በሚፈለገው ቦታና ጊዜ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነው»

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ዓይናችንን ለአፍታ ሳንነቅል ደህንነቱን እየጠበቅን እንገኛለን ሲሉ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጄር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል መንግስት በሚሰጠን ትእዛዝ መሰረት ሀገር ለማፍረስ በሚጥር የትኛውም ኃይል ላይ በሚፈለገው ቦታና ጊዜ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩት፥ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ የውጭ ጫናዎችና የውስጥ ትንኮሳዎች የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተናዎች ሆነው ቆይተዋል።
“ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ተቀናጅተው የተለያዩ ጫናዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል” ነው ያሉት።

የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ወጪ እየገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ በከንቱ ማስቀረት መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ አኳያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው፥ ድሉ መንግስትና ህዝብ አንድ ሆነውና ተናበው ከሰሩ ምን መፍጠር እንደሚችሉ አመላካች መሆኑን አብራርተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በተለይ ሌት ተቀን ግድቡን እየጠበቀ ላለው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረም ተናግረዋል።

አየር ኃይላችን በግድቡ ላይ ሊጋረጡ የሚችሉ “ውጫዊ ስጋቶችን ጠንቅቆ ይገነዘባል” ያሉት ሜጄር ጀኔራል ይልማ።

በዚህም “ዓይናችንን ከግድቡ ላይ ለአፍታ ሳንነቅል ደህንነቱን የመጠበቅ ተልዕኳችንን እንወጣለን” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት በትግራይ ክልል ሃገር ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸባሪ ቡድን ላይ በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ የኢፌዴሪ አየር ኃይል አበርክቶ ጉልህ እንደነበርም ነው ሜጄር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ያስታወሱት።

ለሃገርና ህዝብ ጥቅም ዴንታ የሌለው ኃይል “ሃገር ለማፍረስ በተደጋጋሚ ሞክሮ አልተሳካለትም፤ አሁንም በሚችለው አቅም ሙከራ እያደረገ ይገኛል” ብለዋል።

በመሆኑም አየር ኃይሉ ከመንግስት በሚሰጠው ትእዛዝ መሰረት አገር ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎች ላይ በየትኛውም ቦታ ጥቃት ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል የትኛውንም የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁመና እና ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ሜጄር ጀኔራል ይልማ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲጠብቅ ተደርጎ መደራጀቱን የገለጹት ዋና አዛዡ፥ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከዚህ አኳያ የሰው ኃይል ግንባታን መሰረት ያደረገ ውጤታማ የሪፎርም ስራዎች መከናወኑን ተናግረዋል።

በለውጥ ስራዎች አማካኝነትም ወቅቱን የሚመጥን ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንደተቻለ ጠቅሰው፥ የለውጥ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ግዳጅ ላይ ለሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀው፥ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሜጄር ጀኔራል ይልማ ጥሪ አቅርበዋል። FBC

Exit mobile version