Site icon ETHIO12.COM

«ማሸነፍ ማለት አሸባሪውን ትህነግ ነቅሎ መጣል ነው»

“በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያዝም ሆነ የሚለቀቅ ቦታ የለም” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ እንዳሉት “በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያዝም ሆነ የሚለቀቅ ቦታ የለም፡፡ ለእኛ ጦርነቱን ማሸነፍ ማለት አሸባሪውን ትህነግ ነቅሎ መጣል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቆራጥነት ትግል ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

የህልውና ጦርነት ግብ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ከስሩ ነቅሎ በመጣል ክልላችንን እና ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ ነጻ ማውጣት እንጂ ቦታ በመያዝና መልቀቅ የሚወሰን አይደለም ነው ያሉት፡፡

በእስካሁኑ ሂደት አሸባሪውን ቡድን ደግፈው የዘመቱም ሆነ የሚተማመኑባቸው ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ እየተመቱና ድል እየተደረጉ በመሆኑ ትህነግ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው ብለዋል፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ‹‹ደባርቅን ልይዝ ነው፤ ወልድያ ልገባ ነው›› እያሉ ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም የማኅበረሰቡን ሥነ ልቦና ለመጉዳት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተበላበት እቁብ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

የአማራ ህዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በድጋፍ ሰልፍ፤ ወደ አውደ ውጊያው በመግባትም፤ በገንዘብ እና በአይነትም ለጦሩ ድጋፍ በማድረግ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ ሥነ ልቦናው ከፍ ያለ እና ወትሮም የነበረ የአባቶቹ ስለሆነ በትህነግና በትህነጋውያን የውሸት ፕሮፓጋንዳ አይሸበርም ብለዋል፡፡

አቶ ግዛቸው እንደተናገሩት አሸባሪው ትህነግ በወልቃይትና አካባቢው፣ በዋግኽምራና ራያ ግንባር በከፈተው ወረራ በዛሬው ውሎና ከትናንትና ማታ ምሽት 3፡00 ጀምሮ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ ውጊያው ቀጥሏል፡፡ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ታጋዮች አሸባሪውን ትህነግ ከያለበት ለቅሞ በመምታት ከፍተኛ ድል እያገኙ ነው፤ አሁንም በከፍተኛ ዝግጅትና ውጊያ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡

በትዊተር፣ በፌስቡክና በዩቱዩብ አሸባሪው ትህነግ እያሰራጨው የሚገኘውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመቀልበስ ረገድ እየተደረገ ያለው ርብርብና ትግል ሌላኛው ድል እየተገኘበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግዛቸው አልፎ አልፎ በግንዛቤ ጉድለት ወይም በባንዳነት ለጠላት መረጃ የሚሰጡ ስላሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ በቀጥታ ነፍጥ አንግበው ወደ ጦርነት እንዲሄዱ በመመረቅ ከመሸኘት ባሻገር በገንዘብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ የሞራል ድጋፍ በመስጠት በአጠቃላይ ሀቀኛ ደጀን በመሆን እያደረገው ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአሸባሪው ትህነግ አማራን የማጥፋት፤ ሀገርን የመበተን ዓላማ ተይዞለት ረዘም ወዳለ የትጥቅ ትግል በማስገባት ኢትዮጵያን ለማጎሳቆል የታሰበ ስለሆነ ያለውን ደጀንነት በከፍተኛ መነሳሳትና ወኔ እስከ ፍጻሜ ድረስ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች እና መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በህልውና የማስጠበቅ ዘመቻ በአሉባልታና በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድና ወጥ የሆነ አቋም ይዞ ወደ ጦር ሜዳ መትመም እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

“መንገዳችን አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም እኛን ለማጥፋት የማይተኛውን አሸባሪ ነቅሎ ማስወገድ ብቻ ነው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

Via- አሚኮ

Exit mobile version