Site icon ETHIO12.COM

ስለ ኢትዮጵያ የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን በተደራጀ መንገድ ለመመከት

ኢትዮጵያን አስመልክተው የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን በተደራጀ መንገድ ለመመከት ወጣቱ ተሳትፎውን ማጠናከር እንደሚኖርበት ተገለጸ።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቧን እያገባደደች ባለበት ወቅት ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸው አካላት በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ እያደረጉባት ይገኛሉ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት እያካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ ሳይቀር በዓለም አቀፉ ማኅበሰረብ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዝ በማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃም ቀላል የሚባል አይደለም።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች አገሪቷ የጋጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ለመመከት ወጣቶቸ በአንድነት ልንቆም ይገባል ይላሉ።

ወጣት አዳነ ወርቁ ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረው ተጽዕኖ በገሃድ የሚታይ በመሆኑ ወጣቶች በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ ሳንለያይ በጋራ መመከት ይኖርብናል ሲል ተናግሯል።

ጫናዎችን ለመቋቋም ውስጣዊ ሠላምን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለሠላም መስፈን ወጣቶች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክቷል።

ወጣቱ ሠላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት መከላከልና ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታልም ብሏል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚያሰራጫቸውን ሐሰተኛ መረጃዎች ለመመከት ወጣቱ በትዊተር፣ በፌስቡክና በሌሎች አውታሮች መታገል እንደሚኖርበትም ነው የገለጸው።

ወጣት ቤተልሄም አስረጋኽኝ በበኩሏ አብዛኛውን ጊዜውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፈው ወጣት ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና በመሟገት ሃላፊነቱን መወጣትና ሐሰተኛ መረጃዎችን መመከት እንደሚችል ተናግራለች።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ፍሬህይወት ዳምጠው በበኩሏ ጫናዎችን ለመቋቋም ከመንግሥት ጎን መቆምና መደገፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ወጣቱ ራሱን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊያደርግ ይገባል ብላለች። via ሐምሌ 22 ቀን 2013(ኢዜአ)

Exit mobile version