Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ በጌታቸው አረዳ በኩል የማስተባበያ የሰላም ጥሪ አቀረበ፤ ባድመ ሙሉ በሙሉ ተያዘ

ምስል- የኤርትራ ወታደሮች ባድመ ላይ ቁርስ ሲቆርሱ፣ ለኤርትራ ፕሬስ የተወሰደ

በመግቢያው እንደተለመደው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የወነጀለው የትህነግ መግለጫ የተፈጠረውን ቀውስ በሰላማዊ ንግግር ለመቋጨት ፈቃደኛ መሆኑን አመልክቷል። ከቀናት በፊት ” አዲስ አበባ ለመግባት የሚያግደን ምድራዊ ሃይል የለም” በሚል መልዕክት ሲያሰራጭ የነበረው ጌታቸው በቲውተር አምዱ ላይ ያሰራጨው መግለጫ ቅደም ሁኔታውን ትቶ ትህነግ ድርድር መጠየቁ ከተገለጸ በሁዋላ መሆኑ እንደ ማስተባበያና ደጋፊዎችን ለማበረታታት እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል።

በጀት፣ ህክምና፣ መብራት፣ ስልክ፣ ማንኛውም ትራንስፖርት የእርዳታ መንገዶች ኮሪዶር መከፈት ( የሱዳን ድንበር ይከፈት ማለት ነው) የታሰሩ የትግርያ ተወላጆች፣ በመከላከያ ውስጥ የነበሩና መንግስት በክህደት የያዛቸው እንዲፈቱ፣ የአማራና የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡና አካታች የሽግግር መንግስት እዲቋቋም ሲል ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የድርድር ሃሳብ ቀደም ሲል ድርጅቱ ካወጣው መግለጫ በሁለት ነጥቦች ዝቅ ያለ ነው።

ሕዝብ በምርጫ ያጸናውን፣ የህልውና ዘመቻውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት ከዳር እስከዳር ” መንግስቴ ከጎንህ ነኝ” ብሎ ዓለም እያየ መነሳቱን ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ መግለጫው በመግቢያው መንግስት እንደሌለ ወይም ጊዜው እንዳከተመ አትቷል። አያይዞም ይህንኑ መንግስት “ቀለብ፣ በጀት፣ አገልግሎት፣ መድሃኒት ወዘተ በቅድመ ሁኔታ አሟላልኝ” ሲል ጠይቋል።

በአፋር ግንባርና በራያ በኩል፣ እንዲሁም በማይጸብሪ ግዛቱን አስፍቶ የድርድር አቅሙን ለምሳደግ፣ የጅቡቲ መንገድን በመዝጋት ጫናውን ለማሳደግ የተነቀሳቀሰው ትህነግ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱና ሃሳቡ እንዳልተሳካ፣ በቀጣይ ሁለትና ሶስት ቀናት በርካታ ኪሳራ እንደሚደርስበት በይፋ የሚመለከታቸው ክፍሎች በሚናገሩበት ወቅት የወጣው መግለጫ ለደጋፊዎች ሞራል የተዘጋጀ መሆኑ በመግለጫው ግርጌ ወዲያውኑ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

በሁለት ሳምንት ውስጥ የሰው ክምችት በማሰለፍ ጥቃት የሰነዘረው ትህነግ አስከፊ የተባለ ጉዳት እንደደረሰበት ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ባድመ ኤርትራ ወታደሮቿን አስፍራ፣ ባንዲራዋን ሰቅላ በይፋ በህግ የተፈቀደላትን ቦታ ተቆጣጥራለች። ሟቹ መለስ ዜናዊ መቶ ሺህ ወገኖች ያለቁበትን ጦርነት አልጀርስ ሄደው ባድመን በማስረከብ በሰላም እንዲቋጭ ከተስማሙ በሁዋላ ኤርትራ በሄግ ይግባኝ በሌለው ፍርድ ባድመን ማግኘቷ ይታወሳል። በወቅቱ አዋቂዎች ትህነግ በፍርድ ቤት ለክርከር የያዘው መረጃ እንደሚያስረታው ሲነገረው ” አልሰማም” ብሎ ባድመን ማስረከቡ አይዘነጋም።

ትህነግ በአሜሪካና ሲአይኤ ድጋፍ መንግስት ከሆነ በሁዋላ ራሱን ” ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ” በሚል ቁልምጫ እየጠራ ያካለለውን የአማራ መሬት ከተነጠቀ በሁዋላ ” ወራሪውን የአማራ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ጠራርገን እናስወጣለንና ገና ከአማራው ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ” በሚል ሲወተውቱ ከርመው ከትናት ጀምሮ የንግግር መንገድን በተለያዩ አግባቦች ማስተጋባት የጀመረው ጌታቸው ረዳ ” የኢርትራን ሃይል እንደቁሳለን” ሲል እንደነበርም አይዘነጋም።

“በፕሮፓጋንዳ የተከፈተ ዘመቻ” እንመክት የሚሉ ወገኖች የዲጂታል ጦርነቱን በተቀላቀሉበትና ትህነግ ለሚያሰራጨው የሃሰት ዜና ምላሽ በመስጠት ማክሸፍ ሲጀምሩ፣ በጦር ሜዳ ሰፊ የሚባል ድል በሚሰማበት ወቅት ትህነግ ያቀረበው የመነጋገር ጥያቄ በርካቶችን አስገርሟል።

“መከላከያችንን ያረደ ሃይል ለፍርድ ሳይቀርብ የሚሆን ነገር የለም” የሚል ምላሽ እየተሰጠበት ያለው ይህ የንግግር ጥያቄ ከመነሳቱ በፊት ” ቅደም ሁኔታዎቹን ትቶ ትህነግ ለመነጋገር ተስማማ” በሚል መዘገባችን ይታወሳል። መረጃው ፍጹም ትክክል ሲሆን ትህነግ ያቀረበው ሃሳብ የማንነትና የድንበር ባለቤትነት ያለባቸው ቦታዎች በፌደራል መንግስት ስር እንዲሆኑ፣ የተፈናቀሉ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚል ነው። ለአትላንቲክ ካውንስል ቅርብ የሆኑ የመረጃ ሰዎች እንዳሉት ትህነግ ያቀረበው ጥያቄ በውስጥ የተፈጠረበትን ችግር መቋቋም አለመቻሉ ጭምር ነው።

ለትግራይ ሕዝብ ሲባል አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ቢታመንም በሰሞኑ ጦርነት ብቻ በርካታ ሕጻናትን ጭምር ያስጨፈጨፈው ትህነግ፣ ሲዳከም ማምለጫ ስልት ስለሚነድፍ በርካቶች ጥንቃቄ እንዲደረገ ይመክራሉ።

መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው ትህነግ ስላወጣው መግለጫ ዛሬም ሆነ ቀደም ሲል በይፋ ምላሽ አልሰጠም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሕዝብ ተብሎ የተወሰደን የተናጠል የተኩስ አቁም እንደ ልዩ አጋጣሚ በመጠቀም እዛም እዚህም ትንኮሳ የሚያካሂደው ሃይል ” እጅ አፍ ላይ በሚያስጭን ” ሲሉ በገለጹት ደረጃ ለመምታት በከፍተኛ ሚስጢር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንን፣ ይህ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ህዝብም ዓለምም እንደሚያየው ማስታወቃቸው ያታወሳል። መንግስት በይፋ ከመከላከል ወደ ሙሉ ማጥቃት እንደሚዘዋወር መዘገባችን ይታወሳል።

ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ ስድብ፣ አዲስ አበባ እንገባለን፣ መከላከያ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፣ ደባርቅን ይዘናል፣ ጎንደር እጃችን ላይ ወድቋል፣ ደብረብርሃን እንገባለን … የሚሉ ይዘት ያላቸውና የትህነግ ሃይል ያሻውን ለማድረግ ምድራዊ ሃይል አያቆመውም፣ ሲኦልም ቢሆን በመግባት ጠላቶቹን ያደባያል … የሚል ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ከጌታቸው አሰፋ አምድ ላይ አልታዩም።

በአፋር ግንባር ሶስት ክፍለጦር አሰልፎ የነበረው ትህነግ ከፍተኛ የተባለ ኪሳራ እንደደረሰበትና ያሰበው እንዳልተሳካ በትናትናው ዕለት መከላከያ ማስታወቁ፣ የአማራ ክልል በበኩሉ ” ትግሉ ቦታ መያዝና መልቀቅ ሳይሆን ትህነግን ለመጨረሻ ጊዜ መንቀል ነው” ሲሉ በገጠሙት ግንባር ስትራቴጂካል ድል እያገኙ መሆናቸውን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።


Exit mobile version