Site icon ETHIO12.COM

በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥፋት አንድ አትሌት ከውድድር ተሰረዘች! ጥፋቱን የፈጸሙት ቶኪዮ እየተዛናኑ ነው!!

ጡረተኛው የኢትዮጵያ አትሊቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ሃኪም ዶክተር አያሌው ” ለምን ቶኪዮ ባሻቸው ቀን አልሄዱም” ብሎ ” የመግስት ያለህ” ሲል የነበረው ፌዴሬሽን አሁን ምን ይል ይሆን? ኢትዮጵያን በ800 ሜትር እንድትወክል ፌዴሬሽኑ “ዝግጁ ናት፣ ሁሉንም ጉዳይ አሟልታለች” ብሎ የላካት አትሌት ከውድድር ውጭ መደረጓ ይፋ ሆኗል።

አትሌት ወርቅነሽ መሰለ ከውድድር ውጭ የሆነችው በአገር ውስጥ ለውድድር የሚያበቃትን የዶፒንግ ምርመራ ባለማድረጓ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል። በህጉ መሰረት ማንኛውም አትሌት ከኦሊምፒክ በፊት ለአስር ተከታታይ ወራት በየሶስት ሳምንቱ የአበረታታች መድሃኒት ሙከራ ማድረግ አለበት።

ይህን ደንብ ዶክተር አያሌው ጠንቀቀው ያውቃሉ። በዶፒንግ ኮሚቴ ውስጥም አሉበት። ከዚያም በላይ ስራቸው ነው። በዝግጅት ወቅት ከስልተናው በተጨማሪ ለእያንዳንዱ አትሌት ፋይል ተከፍቶ በዝርዝር አስፈላጊ የህክምና ነክ ጉዳዮች በአግባቡ ስለመካሄዱ የሚያገባቸው እሳቸው ናቸው። ውድድሩ ኦሊምፒክ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀደም ብሎ ዝግጅትና ትኩረት እንዲደረግ መመሪያ ሲሰጡ መንግስት በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች ቢኖሩበትም፣ ምን ያህል ለጉዳዩ ክብደት እንደሰጠ የሚያሳይ ሆኖ ሳለ አሁን የተከሰተው ጉዳይ ግን ስራቸው በአግባቡ መስራት ባቃታቸው ክፍሎች የተሰራ ወንጀል ነው።

አትሌቷ የመጨረሻውን የዶፒንግ ምርመራ ሳታደርግ ፌዴሬሽኑ ፈቅዶላት ዳይመንድ ሊግ ተሳትፋ ተሳትፋለች። ፌዴሬሽኑ ለአስር ወር ለኦሊምፒክ ልዩ ዝግጅት ሆቴል የገቡ አትሌቶች ልዩ ክትትልና በመረጃ አያያዝ የዳበረ ትኩረት እንዲደረግላቸው መሆኑንን ዘንግቶ ወርቅነሽን ” ሩጪ” ብሎ ለቀቃት። ምርመራዋን ሳታደርግ ቀረች።

የሚያሳዝነው ምርመራውን ያጓደለ አትሌት በዓለም ዓቀፉ የጸረ አበርታች ነጥረ ነገሮች ተቆጣጣሪ ኢጀንሲ ( ዶክተር አያሌው አሉበት) ህግና መርህ መሰረት መወዳደር እንደማይችል እየታወቀ፣ አትሌቷን ” ሁሉ ሙሉ፣ ሁሉ ዝግጁ” ብሎ ፌዴሬሽኑ ወደ ቶኪዮ ላካት። በመጨረሻም በቁጥር የሚቆጠሩ ጥቂት አትሌቶችን መረጃ አደራጅቶ መምራት ያልቻለው ፌዴሬሽን በእንዝላልነት የሳተውን ወይም አውቆ ያደረገውን፣ አወዳዳሪዎ አካል ባለው ሲሰተም መሰረት ከሺህ አትሌቶች መካከል ነቅሶ በማውጣት “የሚፈለገውን አላሟላሽም” ብሎ አሰናበታት።

ህግ ምርመራውን ያላሟላ ” ልክ አበረታች መደሃኒት ተጠቅሞ ራሱን እንደደበቀ ” ስለሚያስቆጥር ከተወዳዳሪነት ወደ ተመልካችነት ተዛውራለች። እንዲህ ያለው ጥፋት እጅግ ከባድና አገርን የሚያሳጣ፣በስራው ዘርፍ ያሉት ሃላፊዎችና ተቆጣጣሪዎችን የምግባር ጉድለት የሚያሳይ፣ ከምንም በላይ ለተመደቡበት ሃላፊነት የሚመጥን ስብዕና ጉድለትን የሚያሳይ በመሆኑ ይህን ባደረጉ ላይ ኮማንደር ደራርቱ በቅጽበት የግድ ውሳኔ መወሰን ይገባቸው ነበር። ውሳኔያቸውንም ልክ ” መንግስት የለም” ብለው ለአቤቱታ እንዳሰሙት ስራቸውን፣ ሃላፊነታቸውንና ስልጣናቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ሊያሳዩ ይግባ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን አስመልክቶ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ከየትናውም ወገን የተባለ ነገር የለም።

ለመወነጃጀልና ” ለምን በአንድ ጊዜ ተንጋግተን ቶኪዮ አልገባንም? ዶክተር አያሌው እስካሁን አልሄዱም? ” በሚል በስፍራው ያሉትን ሁለት ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎችን በናቀ መልኩ መግለጫ የሰጠው ፌዴሬሽን ምን ይል ይሆን? አንድ የአሜሪካ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የጃፓን ወይም የኬንያ ሃኪም ይህን ተግባር ቢፈጽም ይህን ጊዜ ሚዲያው ይዘለዝለው ነበር። ጥፋቱ አይሰሩም፣ ከሰሩም እንደ እኛ አገር ባለሙያ አይናቸውን በቸው አጥበው ምክንያት ለመደርደርና ጣትን በሌላ ለመቀሰር አያደቡም። በይፋ ይቅርታ ተይቀው ይለቃሉ።

በአገራችን ጥፋቱን አውቆ የሚለቅ፣ ጥፋተኛውን የሚያባርር ሃላፊ በሁሉም ዘርፍ ስለሌለን እንዲሁ ከነምናምናችን እናዘግማለን። ኬንያ በኢድመንቶን ዓለም ዋንጫ በአስር ሺህና አምስት ሺህ በሁሉም ጾታ በኢትዮጵያ ፍጹም የበላይነት ሲያዝባት የፌዴሬሽኑ ፕሬቪዳንት ልዑኩ ኤርፖርት ሳይደርስ ነው ሙሉ በሙሉ እንደተባረሩ ያስታወቁት።

ለአበልና ለሽርሽር ” ህዝባሽን፣ አገራችን፣ መንግስታችን እወቁልን” በሚል ለቅሶ ሲያሰራጭ የነበረው ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ አፍንጫው መያዝ አለበት። ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ባክኗል። ከዚህም በላይ ዓለም በዝርክርክነታቸን ስቋል። ከመክፈቻው ስነስርዓት ጀምሮ እከክልኝ ልከክልህ ቀርቶ በደንብ መገምገም አለበት። በልቅሶና በእሪታ ሳይሆን በመርህና በአምክንዮ ላይ የተንተራሰ ግምገማ ግድ ነው። ከዚህ ውጭ እዛ ሆኖ ” ህዝቤ” እያሉ በማልቀስና አንጀት በመብላት የሚሆን ጉዳይ አይኖርም። ዝርዝሩን ተከታትለን እናቀርባለን።

ነጻነት ደስታና ሀብታም አለሙ ውድድራቸውን አድርገው ሃብታም አለሙ ወደ ቀጣዩ ውድድር ማለፍ ችላለች።


Exit mobile version