Site icon ETHIO12.COM

“አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል፣ እንድትቆራረስ እና ህልውናዋ ጨርሶ እንዲጠፋ በውጭ ኃይሎች የተቋቋመ ድርጅት ነው” ነባር ህወሓት ታጋዮች

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ አንፃራዊ የቅርጽ እና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ ከማስተናገድ ውጭ ቅኝ ሳትገዛ በነፃነት ለዘመናት የዘለቀችው ልጆቿ ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለያቸው በከፈሉት መስዋእትነት ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን የአሜሪካ ሞግዚት ከነበረችው ላይቤሪያ ውጭ በልጆቿ ደም እና አጥንት ነፃነቷን ያስከበረች አፍሪካዊት ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡

ይህ የነፃነት ታሪኳ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል ሆና እንድትዘልቅ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም በዚያ የነፃነት እና የአሸናፊነት ርካብ ላይ መወሳቷ የሚያበሳጫቸው ምዕራባውያን እና ቅጥረኞቻቸው የሀገሪቱን ውስጣዊ አንድነት የተፈታተኑበት ጊዜ ብዙ ነበር፡፡ የቅኝ ግዛት ሙከራቸው አጥንትን ዘልቆ በሚሰማ ሽንፈት የተደመደመባቸው ባዕዳን ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ማባላት እና መከፋፈል የተሻለ አማራጭ ሆኖ ቀረበላቸው፡፡

አሸባሪው ትህነግም የኢትዮጵያ አፍራሽ ባዕዳን ሥሪት እና ቅጥቅጥ ውጤት አንዱ አካል ነበር፡፡ ወቅቱ የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ሰንደቅ የሆነችውን ሀገር ለመበታተን ከውጭ የተሰጣቸውን የሴራ ፖለቲካ ለማራመድ የውስጥ ባንዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ ዘመቻ ላይ ነበሩ፤ 1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ፡፡

ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ ዛሬ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጠላቶች ሴራ አራማጅ የሆኑት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞቹ በሚያራምዱት “የገንጣይ አስገንጣይ ፖለቲካ” የተቀናጀ የጥፋት ዘመቻ ዛሬ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚፈታተኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በንጉሡም ሆነ በወታደራዊው መንግሥት ዘመን ለሕዝቦቿ የተመቸች ሀገር ነበረች ባይባል እንኳን በዘር የተለያዩበትን እና የሚጠፋፉበትን የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ያራመዱበት ወቅት ግን አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበረው ወታደራዊ መንግሥት ደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ ለሚሰፍን ሰላም፣ እኩልነት እና ማኅበራዊ እድገት ያለውን ፍላጎት በማጤን ለሰላም በሚጥርበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት መሰሪ ተልዕኮ ያላቸውን ምዕራባውያን እና የግብጽን ዓላማ ያነገቡ ኃይሎች ከውስጥ ጦርነት ከፈቱ ይላሉ የቀድሞው የህወሓት አባል አቶ አብርሐም ያየህ እና አቶ ገብረ መድህን አርአያ፡፡

ሁለቱ የቀድሞ የህወሓት አባላት ስለሽብርተኛው ትህነግ ሲመሰክሩ ዓላማውን ለማሳካት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ከሚፈጽሙት ጭፍጨፋ በተጨማሪ የሕዝቡን አንድነት እና የሀገር ፍቅር ስሜትን ለመስለብ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት በህቡዕ ከፍተውበትም ነበር፡፡ ራሱን “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ” ብሎ የሰየመው ጠባብ ብሔርተኛ ቡድን የተቀበለውን ኢትዮጵያን የመበታተን አደራ ለማስፈጸም በአንድነት ተሳስረው በኖሩ ብሔሮች መካከል ጥላቻን በመፍጠር የእርስ በርስ ጦርነት ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱንም አውስተዋል፡፡

አቶ አብርሐም ያየህ እና አቶ ገብረ መድህን አርአያ “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና ይህንን በሽብርተኛው ትህነግ እና በተባባሪዎቹ የተጠነሰሰውን ሀገርን የመከፋፈል ሴራ ለኢትዮጵያውያን እና ቀሪው ዓለም በተደራጀ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች በወርሃ ጥቅምት 1982 ዓ.ም በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት እውነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ አድርገውት ነበር፡፡

አቶ አብርሐም ያየህ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት ብለው ከሚያምኑት ተራማጆች መካከል አንዱ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ለለውጥ ሲባልም ከተማሪዎች እስከ ሠራተኞች ንቅናቄዎች ድረስ ገብተው ለመታገል ሞክረዋል፡፡ ሙከራቸው ሁሉ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ምንም እንኳን ጥልቅ የርዕዮተ ዓለም መራራቅ ቢኖራቸውም በሂደት ይስተካከላል በሚል እሳቤ በየወቅቱ እና ሂደቱ ስሙን እና ግብሩን የሚቀያይረውን ሴረኛ ቡድን የያኔውን ማገብት (ማኅበረ ገስግስቲ ብሔረ ትግራይ) የአሁኑን ትህነግ ተቀላቀሉ፡፡ አቶ አብርሐም “ህወሓትን ኢትዮጵያዊ መልክና ቁመና ለማስያዝ የተደረገው ጥረት አልተሳካም ነበር” ብለዋል በምስክርነታቸው፡፡ በመጨረሻም ሽብርተኛው ትህነግ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የመጣል ሴራ ሲገባቸው እነዚህ ነባር ታጋዮች ራሳቸውን ከድርጅቱ አገለሉ፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ ከመነሻውም ለትግራይ ሕዝብ ችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት የተቋቋመ ድርጅት አልነበረም ብለዋል አቶ አብርሐም ያየህ፡፡ በቀጥታ ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል፣ እንድትቆራረስ እና ህልውናዋ ጨርሶ እንዲጠፋ በውጭ ኃይሎች የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በሽሬ አካባቢ ደደቢት በርሃ ውስጥ ለትጥቅ ትግል ሲገባ ግብሩን መቀየሩን ይናገራሉ፡፡

እነ መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት ሱዳን ላይ በነበረ ዝግጅት “የትግራይን ሪፐብሊክ እንመሰርታለን፤ የምንታገለውም ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥለን ራሷን የቻለች ታላቋን ሪፐብሊክ ትግራይን ለመመስረት ነው” ብለው ነበር የሚሉት ግለሰቦቹ ይህ በርካታ የወቅቱ አባላትን ቅራኔ ውስጥ ከትቶ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ ጉዳዩ በአባላቱ ዘንድ የመወያያ አጀንዳ እና የቅራኔ ምንጭ በመሆኑ እነአቶ መለስ “ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው ስለማይተማመኑ እና ለየብቻ መታገል ስላለባቸው ነው፤ የሪፐብሊኩ ምስረታም እስከ መገንጠል ይደርሳል” የሚል ማወናበጃ መልስ ሰጥተው ነበር ይላሉ፡፡ ይህም ሽብርተኛው ትህነግ ገና ከጅምሩ በሐሰት ትርክት፣ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና በክህደት የጎለመሰ ድርጅት እንደነበር ማስረጃዎችን ጭምር ጠቅሰዋል፡፡

ማገብት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ በጥርጣሬ እየታየ መምጣቱን ተከትሎ በወቅቱ የድርጅቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ የነበሩት መለስ ዜናዊ አዲስ ስያሜ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ ተሓሕት (ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ) ትግራይን በጠባብ ብሔርተኝነት ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተለየ አድርጎ የማንጸባረቅ እንቅስቃሴ መጀመሩን የቀድሞ አባላቱ ገልጸዋል፡፡ ይህም ድርጅቱ በሕዝብ ዓይን ውስጥ ጥርጣሬ ላይ በመውደቁ ትግራይን ነጥሎ ተጠቂ እና ተጎጂ አድርጎ የመሳል ስትራቴጅ በስፋት ለመንዛት ምቹ ሆነላቸው፡፡ ይህን መሰል የሽብርተኛው ትህነግ ሕዝብን የመጨፍጨፍ ስትራቴጂ እስከ አይደር ትምህርት ቤት ጭፍጨፋ ድረስ ስር የሰደደ እንደነበር አውስተዋል፡፡

ተሓሕት የሚለው መጠሪያም ብዙ ሳይቆይ ወደ ህወሓት (ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ) እንዲቀየር ግድ አለው፡፡ “ወያኔ” የሚለው ቃል ከጥንት ጀምሮ በትግራይ የነበረ የትግል ስያሜ እንደነበር ነባር ታጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡ በወቅቱ ሌላውን የትግራይ አካባቢ “ትግሉ የአንተም ጭምር ነበር” ለማለት የቀረበ ማወናበጃ ስያሜ ነበር ነው የሚሉት፡፡ የእንደርታን ጨምሮ የኢሮብን እና የሌሎችን ትግራይ አካባቢዎች ተቃውሞ ለመሸወድ የቀረበ ስያሜ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሽብርተኛው ትህነግ በሦስት አስርት ዓመታት የመሪነት ቆይታው የትግራይን ሕዝብ ብሎም መላው ኢትዮጵያን አጎሳቁሎ ነው ያለፈው፡፡

በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንኳን እታገልለታለሁ የሚለው ሕዝብ በተደጋጋሚ ድርቅ እንዲጠቃ የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዳይሠራ አድርጓል፡፡ በስሙ በርካታ የገንዘብ እና የዓይነት እርዳታ ከምዕራባውያን እየለመነ ለራሱ ፍጆታ አቅርቦታል፡፡ በድጋፍ የሚመጣው ስንዴ እና ዘይት ሱዳን ገበያዎች ለጉድ ይቸበቸቡ ነበር፡፡ ገንዘቡን መሳሪያ ይገዛበታል፤ ተጠቃህ እያለ የደሃውን ገበሬ ልጅ በጦርነት ይማግዳል፤ ራሱን፣ ልጆቹንና ዘመዶቹን በውጭ ሀገራት እንደልቡ እየተንቀሳቀሰ ቅንጡ ኑሮውን ይመራል፡፡

እንደ ቀድሞ አባላቱ መረጃ ሽብርተኛው ትህነግ በስልጣን ዘመኑም የደገመው ያንኑ ነው፡፡ ዛሬ የምናየው የሽብርተኛው ትህነግ ክህደት ከትናንቱ የቀጠለ እንጂ በአንድ ጀምበር የተፈጠረ አልነበረም፡፡

ፕሬዚዳንት ዚያድባሬን አግዞ ኢትዮጵያን የወጋው ትህነግ ዳግም ኢትዮጵያን ሲኦልም ቢሆን ወርደን እናፈርሳለን ሲሉ መስማት አዲስ ልክፍት ተደርጎ መውሰድ የለበትም፡፡ ቀጭን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ያላቸውን የትግል አጋሮቹን ለመሳሪያ ሲል ጋብዞ እና አቅፎ ስሞ ምሽት ላይ ጨፍጭፎ የሄደ አካል ነው፡፡ ለዓመታት ከውጭ ጠላት ሲጠብቀው የነበረውን እና የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሲሰጠው የነበረውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝን በክህደት ያጎረሰ እጁን ሲነክስ ብርቅ የሆነው ለኛ ነው እንጂ ቡድኑ ክህደት ጥርሱን የነቀለበት ነው፡፡ አይደርን ጨምሮ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች “የዓላማ ጽናት” በሚል ክህደት የጨፈጨፈና ያስጨፈጨፈ ቡድን ህጻናትን ለጦርነት ቢያሰማራ፣ የሰብዓዊ ቁሳቁስ ቢያግድ እና ስደተኞችን ቢያጠቃ አይገርምም፤ ምክንያቱም የኖረበት ሴራ በመሆኑ ነው፡፡ አማራጩም አንድ ነው እርሱም አረሙን ከማሳው ላይ ማንሳት፡፡
ምንጭ፡- የወያኔው ሴራ በቀድሞ አባላቱ ሲጋለጥ (1982 ዓ.ም)

በታዘብ አራጋው ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version