Site icon ETHIO12.COM

የባይደን ፖሊሲ | ሳማንታ ፓወር እና የኢትዮጵያ ጉዞ


– የዓባይ ፡ ልጅ

የ USAID ዋና ሃላፊዋ ሳማንታ ፓወር ዛሬ ሱዳን እንደሚገቡ ተገልጿል። በአምስት ቀናት ቆይታቸው ወደ ኢትዮጵያም የሚመጡ ይሆናል። ወይዘሮ ፓወር እንደስማቸው በጦር አውርድ ፍልስፍናቸው ነው የሚታወቁት። ዋሽንግተን በአለም ዙሪያ ሰብአዊ መብት ተጥሷል የሚል ፍርጃዋን ተከትሎ መደረግ በሚኖርበት ርምጃ ላይ የሴትዮዋ አቋም ገዢ ስለመሆኑም ይነገራል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሳማንታ ፓወር “የአሜሪካ ልዕለ ሀያልነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመዋጋት ላይ መዋቀር አለበት ባይ ናቸው። ለዚህም አሜሪካ ጦሯንና ያላትን አቅም ሁሉ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ትግል ማዋል አለባት” የሚለው ብርቱ አቋማቸው ይለያቸዋል።

ፓወር የሀርቫርድ መምህር ነበሩ። ፕሬዝደንት ኦባማ በዘመነ ስልጣናቸው የውጭ ጉዳይ አማካሪ አደረጓት። የኦባማ ቅርብ ሰው የሆኑት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ደግሞ በ USAID ሀላፊነት ሾሟት። USAID የተባለው ድርጅት በተለይም በዘመነ ባይደን ከአሜሪካ የውጭ ፖሊሲና ከብሄራዊ ደህንነት ጋር እንዲቀናጅ ሆኗል።

ለትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ ዕርዳታ ካልቀረበ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የቅጣት ርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትችል አንድ የ ዩኤስአይዲ ከፍተኛ ሃላፊ ለሮይተርስ በተናገሩበት ዕለት ሳማንታ ወዲህ ለመምጣት ዕቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል። ጉዟቸው ወደ ትግራይ የሚደረገው ርዳት ያለምንም እገዳ እንዲደርስ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ነው ተብሏል።

በአዲስ አባባ ከተማ በትግራይ ተወላጆች ላይ ይፈጸማሉ የተባሉት ጅምላ እስሮች አሜሪካን እንዳሳሰባት የጠቆሙት ሃላፊ፣ የትግራይ ተወላጆች በማንነታቸው ተለይተው የብሄር ማጽዳት ወንጀል ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ተነግሯል። መግለጫው የሳቸው ስለመሆኑ ይገመታል።

በሌላ በኩል ሳማንታ ፓወር በትዊተር ገጻቸው ስለትግራይ ጉዳይ ስሜታዊ የሆኑ መልዕክቶችን ሲፅፈ ነበር። በተለይም የ JUNE 9 ፖስታቸው pinned በማድረግ አናት ላይ ነው ያስቀመጡት።
የራሷ ጦር አውርድ አመል ትዕቢቷ አስረስቷት የሌላ ሉዓላዊ አገር መሪን በመዝለፍም የሚታወቁ ናቸው። በመሰል አነጋገራቸው የኢትዮጵያን መንግስት “ከሰላም ይልቅ ጦርነትን የሚመርጥ” በማለት መናገራቸውንም ታዝበናል።

ፓወር ከጦር አውርድ ፍልስፍናቸው በተጨማሪ አሜሪካ ለሰብአዊ መብት ጥሰት በውጭ አገራት ስለምታደርገው የሃይል ጣልቃ ገብነት (Responsibility to Protect – R2P) የተባለው መርሆ ተግባራዊ እንዲሆን ትልቁን ድርሻ ያዋጡ ናቸው። R2P በተለይም በሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ዘመቻ ያልተሳካውን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በማገናዘብና አተገባበሩን በመለወጥ የተቀረፀ ፅንሰ ሐሳብ ነው። በጣም ጥቂት ወታደሮችና በኃይል አጠቃቀሙ ላይም ብዙ ገደቦች የነበሩበትን የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በመገምገም ነበር በአዲስ ገደብ የለሽ ጠንካራ አካሄድ የተተካው። ፅንሰ ሐሳቡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች አቅሙ ያላቸው አጋር አገራት በውጭ አገራት የመብት ጥሰት የገጠማቸውን ሰዎች የመታደግ ኃላፊነት አለባቸው” በሚለው መርሆ የተቃኘ ነው። ይህን ተከትሎም “ጅምላ ጭፍጨፋን በሃይል በመጋፈጥና በጣልቃ ገብነት መፍታት” ያለ ገደብ እንዲተገበር አቋም ተደረገ።

ጣልቃ ገብነቱ በአንድ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ድርጊቶችን ሁሉ የሚያመላክት ሲሆን የኢኮኖሚ ማዕቀብና ርዳታና ብድር ማቋረጥ፣ ተቃዋሚ ኃይሎችን መደገፍ፣ የሳይበር ጥቃቶች ማድረስ፣ እንዲሁም ከአየር ጥቃት እስከ ወታደራዊ ወረራ ሊደርስ እንደሚችል ያስቀምጣል።

በባራክ ኦባማ በሁለተኛው የስልጣን ዘመን በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን ለሰሩት ሳማንታ ፓወር “ሰብአዊ ጣልቃ ገብነት” ስትል የምትጠራውን በውጭ አገራት የሚደረግ ጣልቃ ዪግባት ርምጃ ቅቡላዊ ይሆን ዘንድ ሕይወቷን ፈጅታበታለች ይባላል። በአብዛኛው ተሳክቶላትም መርህ ሆኖ ይገኛል። ዩናይትድ ስቴትስ ለመላው ዓለም “አስፈላጊ ሀገር” እንደመሆኗ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ወይም ለማቆም ወታደራዊ ብቃቷን የመጠቀም የሞራል ግዴታም አለባት” ትላለች ፓወር። ፓወር በ 1990 ዎቹ በተደረገው የባልካን ቀውስ ላይ የጦርነት ዘጋቢ ነበረች። የፑልትትዘር ሽልማት አሸናፊ ያደረጋት “Problem from hell” መፅሐፍ ደራሲ ነች። መፅሐፉ ስለ አለማቀፍ የመብት ጥሰት፣ ሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲሁም አሜሪካና አጋሮቿ መውሰድ ስለሚገባቸው ርምጃ የሚያትት ነው።

የባይደን ቁልፍ ሰው የሆኑት ባራክ ኦባማ “በውጭ ፖሊሲ ላይ ካሉ 4 ታላላቅ አሰላሳዮቻችን ውስጥ ፓወር አንዷ ነች” እንዳሉላትም አዚጋ ማስታወስ ያሰፈልገናል።
እንደ ሕግ ፕሮፌሰሩ አዚዝ ራና አይነት ምሁራን ደግሞ የፓወልን አቋምም ሆነ ደቀመዛሙርቷ የሆኑ ባለስልጣናትን “የአሜሪካን ኢምፔሪያሊስታዊ አካሄድ ለመሸፋፈን ሰብአዊ መብትን እንደ ካርታ የመጠቀም “War Hawk” አካሄድ ይሉታል።

ሳማንታ ፓወር 2008 እኤአ ከፓስፊክ ስታንዳርድ እና ሚለር-ማኬን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “War hawk” አይደለሁም “Human Right Hawk” ነኝ በማለት ሞግተዋል። በዚህም “አሜሪካ የሰብአዊ መብት መርሆዎችን በአንክሮ ልትከታተልና የዘር ማጥፋትና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመዋጋት ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አለባት” የሚል አቋማቸውን አንፀባርቀው ነበር።

ለጆ ባይንደን መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሳይበር ደህንነትና በዓለም አቀፍ ህጎች ላይ በተመሠረተ ቅደም ተከተል ቻይናና ሩሲያ ላይ ያነጣጠረ የውጭ ፖሊሲ ስለመከተል ነው ከሹመታቸው ማግስት አንስተው ሲገልፁ የሚደመጡት። በባይደን ፖሊሲ አሜሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከነበረችበት የፀረ -ሽብርና የውጭ ጣልቃ ገብነት የመራቅ ፍላጎታቸው ማሳያ ስለመሆኑ እንጀ ቪቪያን ሳላማ ያሉ ተንታኞች ያስቀመጡት ነው።

ጆ ባይደን “የአሜሪካን መፃኢ ጥቅም ለማስጠበቅ የኛን አካሄድ ከሚቀበሉ አገራት ጋር ወዳጅነታችንን ማጠናከር እና በጋራ መሥራት አለብን” ሲሉ የተደመጡትም ከሳምታት ወዲህ ነው።

የተጠቀሱት ጉዳዮች ባለበት ሁኔታ ውስጥ ዛቻቸውን በማስቀደም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እመጣለሁ ያሉት ሳማንታ ፓወር ጋር በምን ልንስማማ እንችላለን? ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመኔ ፀፀት ያሉትን የሊቢያ ጣልቃ ገብነት በዋናነት ጎትጉተው ያሳመኑት እኚሁ ሳማንታ ፓወር ነበሩ። በሶሪያም በተመሳሳይ ጎትጉተው ባራክ ውድቅ ቢያደርጉትም።

(ሴትዮዋ ጦርነት ላይ ለምን ሙጭጭ አለች የሚለው ጥያቄ ያጭራላ? እመጣበታለሁ)

የሆነ ሆነና ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሳማንታ ፓወርን በሰብአዊ መብት ወደ ወቀሷት አገራችን በዚህ ወቅት ለምን መላክ መረጡ? ባይደን ለሴትዮዋ ጦረኛ አቋም የሚኖራቸው አቀባበል ኦባማ ስለ ሊቢያ እንደተቀበሏት? በሶሪያ ሰምተው ችላ እንዳሏት? ወይስ ኢትዮጵያን በ Like Minded መርኋቸው አግባብተው ወዳጅነታቸውን ማጠናከር?

ከመግባባት ሳይደረስ ቢቀር ከአሜሪካ ተገዳዳሪ አገራት ጋር ፈጣን ስትራቴጂክ ትብብር መፈራረም? ኢትዮጵያ የነብዩ(ሠ.ዐ.ወ) ዱዓ ይጠብቅሽ

esleman abay የዓባይ ልጅ

Exit mobile version