Site icon ETHIO12.COM

ሱዳን፣ የህወሃት የሽብር ቡድንን በመደገፍ ለሽብር እያደራጀች ቢሆንም በክልሉ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው


ሱዳን፣ የህወሃት የሽብር ቡድንን በመደገፍ ለሽብር ተልዕኮ እያደራጀች ቢሆንም በክልሉ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ክትትል እየተደረ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ እንዳሉት የህወሃት የሽብር ቡድን በመንግስት የተሰጠውን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ መንግስትን ያሸነፈ በማስመሰል ራሱን በሌላ የሽብር ሴራ ውስጥ ማስገባቱን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በሱዳን የደረሰው የፖለቲካ ቀውስ እልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን ውለታ በመዘንጋት የህወሃት የሽብር ቡድንን በመደገፍ ለሽብር ተልዕኮ ከመቃብር እንዲነሳ እያደራጀች እንደምትገኝ እናውቃለን ብለዋል-ምክትል የቢሮ ኃላፊው፡፡

እናም የሽብር ቡድኑ መነሻውን ሱዳን አድርጎ ከሀገር ውስጥ ካሉ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ያለሙትን የሽብር ተልዕኮ ሳይሳካ ለማክሸፍ ክልሉ ከሱዳን ጋር በሚጋራው ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችን፣ የክልሉን የፀጥታ ኃይሎችን ከፌደራል ፖሊስና ከሀገር መከላከያ ጋር ተቀናጅተው ክትትል እያደረጉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የአሸባሪው ህውሃት ቡድን ንብረቶች እንዲታገዱ እየተሰራን ነው ያሉት አቶ ሙሳ በሽብር ቡድኑ ግብረ አበሮቻቸው ከህግ አግባብ ውጭ ተይዘው የቆዩ የመሬትና ሌሎች ንብረቶችም እንዲታገዱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ በህገ-ወጥ መንገድ ላይ ተሰማርተው የተገኙ ታርጋ የሌላቸው 40 ሞተር ሳይክሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት ምክትል ኃላፊው ታርጋ ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ ተሽካርካሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉም መመሪያ ተላልፏል ብለዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የማዳያ ባለቤቶች ከማዳያ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ጋር በመመሳጠር ህዝቡን ለማማረር እየሰሩት ባለው ህገ-ወጥ ድርጊት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በጥናት የተደገፈ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በየትኛውም አካባቢ ቤት የሚያከራዩ ነዋሪዎችም የተከራዬቻቸውን ማንነት የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ሙሳ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

Exit mobile version