Site icon ETHIO12.COM

ኤርትራዊያን ስደተኞችን ከትግራይ ክልል ለማስወጣት የአደጋ ጊዜ እቅዶች መሰናዳቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ስደተኞቹን የተሻለ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ለማዘዋወር የአደጋ ጊዜ እቅድ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ እየተገነባ ወደሚገኘው አዲስ ጣቢያ እንደሚዘዋወሩ ተቋሙ ገልጿል።

ይህ በ91 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው የመጠለያ ካምፕ 25 ሺህ ስደተኞችን ለማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውም ታውቋል።

እስከ አሁን ድረስ 98 ስደተኞች አዲሱ መጠለያ ወደሚገነባበት አካባቢ የተወሰዱ ሲሆን፤ የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች እየቀረቡላቸው እንደሆነ የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ነቨን ከርቨንኮቪክ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ የዚህን አዲስ የስደተኞች ካምፕ ግንባታ ከጥቂት አጋሮች ጋር በመሆን መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

ከሳምንታት በፊት ኤርትራውያን ስደተኞች እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ እና ለወደፊቱም የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው በመገልጽ መብታቸው እንዲከበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ አበባ ውስጥ መካሄዱ አይዘነጋም።

የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ አሁን ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር እነሱም ይሁን አጋሮቻቸው በአሁኑ ወቅት ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ ለመድረስ አልቻሉም።

የደኅንነት ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ግን ስደተኞችን ከአካባቢው ለማስወጣት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች ማስቀመጣቸውን አስረድተዋል።

በሕብረተሰቡ ትብብር የጋራ ማረፊያዎችን የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ የትራንስፖርት፣ የውሃ፤ የኤሌክትሪክ፣ የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም የምግብ አቅርቦት የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑንም አክለዋል። via -ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

Exit mobile version